ሚያዝያ 09/2013 (ዋልታ) – በ6ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ የሚሳተፉ ፓርቲዎች ስሜት ቀስቃሽና ግጭትን ከሚያጋግሉ የቅስቀሳ ስልቶች ሊታቀቡ እና አገርን ከለየለት ትርምስ የመታደግ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡
የሕግ አማካሪና ጠበቃ አቶ ኃይለማርያም ተመስገን እንደገለጹት፣ አንዳንድ ፓርቲዎች ተፎካካሪዎቻቸውን ለመብለጥ ሲሉ ብቻ ሕዝብ እና ሕዝብን ሊያጋጩ የሚችሉ ስሜት ቀስቃሽ የሆኑ የቅሰቀሳ ስልቶችን ይከተላሉ፡፡
ይህም ሀገሪቱ አሁን ካለችበት ችግር አኳያ ወደለየለት ትርምስ ውስጥ ሊከታት የሚችል በመሆኑ፤ ፓርቲዎች ከጊዜያዊ ጥቅማቸው ባለፈ ለአገር ህልውና ቀጣይነት ታሳቢ አድርገው ሊንቀሳቀሱ ይገባል ብለዋል፡፡
“ከዚህ ቀደምም በነበሩት ምርጫዎች በገዢው ፓርቲም ሆነ በተፎካካሪዎች በጣም ስሜት ቀስቃሽ የሆኑ፣ ለግጭት የሚገፋፉ ቅስቀሳዎችን አይተናል፤ ይሄ ጠቃሚ አይደለም፤ ለራሳቸው ለፓርቲዎቹም ቢሆን የሚጠቅም አይደለም” የሚሉት አቶ ኃይለማርያም፣ ከዚያ ይልቅ ፓርቲዎቹ መወዳደር መቻል ያለባቸው በሃሳብ ጥራት ላይ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
ፓርቲዎቹ የሚመሩባቸው ሃሳቦች በሀገር አስተዳደርና በሀገር ልማት ሊኖራቸው የሚችለውን ውጤት መሠረት አድርገው ሃሳባቸውን መሸጥ አለባቸው ሲሉም አክለዋል፡፡
የምርጫ ቅስቀሳ ከፍተኛ የሆነ ጨዋነት እና ስክነት የሚፈልግ ነው ያሉት አቶ ኃይለማርያም፣ መሪዎቹ የሚያራምዱት አቋምና የፖለቲካ አቋማቸውን ለማራመድ የሚጠቀሙበት ስልት ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል ብለዋል፡፡ ለዚህም የመጀመሪያው ኃላፊነት የፓርቲዎቹ እንደሆነ መግለፃቸውን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘገባ ያመለክታል፡፡