ፓዝ ፋይንደር ኢንተርናሽናል ለጤና ተቋማት የህክምና መሳሪያዎች ድጋፍ አደረገ

መጋቢት 21/2014 (ዋልታ) ፓዝ ፋይንደር ኢንተርናሽናል የተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ለሚገኙ የጤና ተቋማት 6 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ወጭ የተደረገባቸውን የሕክምና መሳሪያዎች ድጋፍ አደርጓል።

የድርጅቱ የክላስተር አስተባባሪ መብራት ከበደ እንደገለፁት ድርጅቱ ባለፉት ሁለት ወራት በብሔረሰብ አስተዳደሩ ጉዳት ለደረሰባቸው የጤና ተቋማት የ11 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የመድኃኒትና የሕክምና መሳሪያዎችን ድጋፍ አድርጓል።

አሁንም 6 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸውን የሕክምና መሳሪያዎች ለጤና ተቋማት ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።

ድጋፉ ለአምደወርቅ እና ፅፅቃ ሆስፒታሎች እንዲሁም በ24 ጤና ጣቢያዎች የእናቶችና ህፃናትን ሞት ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑን አመልክተዋል።

በድጋፉ የላቦራቶሪ፣ የማዋለጃ፣ የመተንፈሻ መርጃና የደም ግፊት መለኪያ መሳሪያዎች፣ ዊልቸር፣ የህፃናትና የአዋቂዎች አልጋ እንዲሁም ከአንገት በላይ መመርመሪያ መሳሪያዎች እንደተካተቱ መግለፃቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

አስተባባሪው እንዳሉት ድርጅቱ ካደረገው የሕክምና መሳሪያ ድጋፍ በተጨማሪ በተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎች ላይ የእናቶችንና ህፃናትን ጤንነት ለማስጠበቅ ባለሙያዎችን ቀጥሮ እያሰራ ይገኛል።