ግንቦት 03/2013 (ዋልታ) – የኢፌዲሪ ፕሬዚደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንትና የአፍሪካ ህብረት የወቅቱ ሊቀመንበር ፌሊክስ ሲሽኬዲን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ፡፡
በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት በቆይታቸው በሁለቱ ሀገራት የጋራ፣ ቀጣናዊና አህጉራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከተለያዩ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ጋር ይመክራሉ፡፡
ፕሬዚደንቱ በተለይም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር ዙሪያ እና የአፍሪካ ህብረት የሚመራው የሦስቱ አገራት ድርድር እልባት የሚያገኝበትን ሂደት ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በዚህም የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን ማብራሪያ ይሰጣቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ፕሬዚደንት ፌሊክስ ሲሽኬዲ ሰኞ ማምሻቸውን ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ሲሆን፤ ከፕሬዚደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጋር ከመወያየታቸው አስቀድሞ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ጋር መክረዋል፡፡
(በአስታርቃቸው ወልዴ)