ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አባላት ጋር ተወያዩ

ሐምሌ 7/2014 (ዋልታ)ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በዛሬው ዕለት ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አባላት ጋር ተወያይተዋል።

ኮሚሽኑ ላለፉት 4 ወራት ወደ ሥራ ከገባ በኋላ ያከናወናቸውን ዋና ዋና ተግባራት ለፕሬዝዳንቷ አብራርቷል።

በተለይም በቅድመ ዝግጅት ሂደት ላይ የሚገኘው ኮሚሽኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር የተለያዩ ውይይቶችን ማድረጉን የኮሚሽኑ ሰብሳቢ መስፍን አርአያ (ፕ/ር) ተናግረዋል፡፡

ከክልሎች እና ቁልፍ ከሆኑ ባለድርሻ አካላት ጋር የመምከር እንዲሁም ለምክክሩ መሰረታዊ የሆኑ ንድፈ ሀሳቦችን የማዘጋጀት ተግባራት እየተከናወኑ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

ኮሚሽኑ የተጣለበትን አደራ እና ኃላፊነት በገለልተኝነት እንዲወጣ ድጋፍ እንዲደረግለትም መስፍን ጠይቀዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በበኩላቸው በኢትዮጵያ በቀጣይ የሚካሄደው ሀገራዊ ምክክር ለሌሎች አገራት ጭምር በምሳሌነት የሚጠቀስ እንዲሆን ኮሚሽኑ ያለምንም ጫና ኃላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡

ለዚህም ለኮሚሽኑ አስፈላጊው ድጋፍና ትብብር እንደሚደረግም ፕሬዝዳንቷ አረጋግጠዋል፡፡

በተለይም ሀገራዊ ምክክሩ ላለፉት 2 ዓመታት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ያጋጠሙ አለመረጋጋቶች፣ የዜጎች መፈናቀል እና ጉዳትን ለመከላከል ትልቅ ተስፋ የተጣለበት መሆኑን ጠቅሰው፤ ኮሚሽኑ ሚናውን እንዲወጣ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢብኮ ዘግቧል።