ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ከአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ጋር ተወያዩ

ታኅሣሥ 8/2014 (ዋልታ) ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በኮትዲቯር የስራ ጉብኝታቸው ከአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት አኪንውሚ አዴሲና (ዶ/ር) ጋር ተወያይተዋል፡፡
በትላንትናው ዕለት በአቡጃን በሚገኘው የባንኩ ዋና መሥሪያ ቤት ባደረጉት ውይይት በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታዎች እና ከኮቪድ-19 በኋላ ቅድሚያ በሚሰጣቸው የልማት ሥራዎች ላይ መክረዋል።
ፕሬዘዳንት ሳህለወርቅ በውይይታቸው ወቅት ባንኩ በበርካታ መስኮች የኢትዮጵያ የልማት አጋር መሆኑን ገልጸው ባንኩ በኢትዮጵያ ልማት ውስጥ እያበረከተ ያለውን ከፍተኛ ሚና አድንቀዋል።
በተለይም በግብርና፣ ትራንስፖርት፣ ኢነርጂ እና የውሃ ዘርፎች ኢትዮጵያ ከባንኩ የምታገኘው አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ድጋፍ ለኢትዮጵያ እጅግ አስፈላጊ መሆኑንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በከባድ ሁኔታዎች ውስጥ ብታልፍም ብሩህ ተስፋ ማሳየቷንና በተለይም አዳዲስ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለበርካታ ወጣቶች ተስፋ መስጠታቸውንም ጠቅሰዋል።
ባንኩ የተለያዩ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን እየደገፈ መሆኑን የገለፁት አደሲና (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ውስጣዊና አካባቢያዊ ሠላምን ለማረጋገጥ የምታደርገውን ጥረት የአፍሪካ ልማት ባንክ በተቻለው ሁሉ እንደሚደግፍና ከኢትዮጵያ ጋር እንደሚቆም ማረጋገጣቸውን ከአፍሪካ ልማት ባንክ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል