ፕሬዝዳንት ባይደን ራሳቸውን ከምርጫ በማግለላቸው የሀገራት መሪዎች ምን አሉ?

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ራሳቸውን ከዘንድሮው ምርጫ ማግለላቸውን እና ድጋፋቸውን ለምክትላቸው ካማላ ሃሪስ እንደሚሰጡ መግለጻቸውን ተከትሎ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች መልዕክት እያስተላለፉ ነው፡፡

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልዶሚር ዘሌንስኪ ውሳኔውን “ፈታኝ ነገር ግን ጠንካራ ውሳኔ” ሲሉ ገልጸውታል፡፡

ዘሌንስኪ “ለፕሬዝዳንት ባይደን አመራር ከፍተኛ አድናቆት አለኝ፤ ሀገራችን ፈተና ውስጥ በነበረችበት ወቅት ከጎናችን ሆነው ረድተውናል። የአሜሪካ ጥንካሬ እንደሚቀጥል ተስፋ እናደርጋለን” በማለት በኤክስ ገጻቸው ሀሳባቸውን አጋርተዋል፡፡

የባይደንን ውሳኔ ተከትሎ ክሬሚሊን እንቅስቃሴዎችን በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን ገልጿል።

የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ “ምርጫው ገና አራት ወራት ይቀሩታል በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ ብዙ ሊለወጡ የሚችሉ ነገሮች ይኖራሉ፤ ታጋሽ መሆን እና የሚሆነውን በጥንቃቄ መከታተል አለብን፤ ለእኛ ቅድሚያ የሚሰጠው ያለንበት ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ባይደን ለእርስዎ እና ለነበረዎት ቁርጠኛ አመራር እናመሰግናለን ያሉት የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኔዝ በዘመንዎ ለዲሞክራሲያዊ እሴቶች፣ ለዓለም አቀፍ ደህንነት፣ ለኢኮኖሚ ብልጽግና እና በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ ባለን የጋራ ቁርጠኝነት ሕብረታችን የበለጠ ጠንካራ ሆኗል ብለዋል፡፡

የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር የባይደንን ውሳኔ እንደሚያከብሩ ገልጸው በሥራ ዘመናቸው አስደናቂ ነገሮችን አከናውነዋል፤ አሁንም ለአሜሪካ ሕዝብ ይጠቅማል ያሉትን ውሳኔ ወስነዋል ሲሉም አክለዋል፡፡

የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ በበኩላቸው “ፕሬዝዳንት ባይደንን ለብዙ ዓመታት አውቀዋለሁ፣ እርሱ ታላቅ ሰው ነው፣ የሚያደርገው ነገር ሁሉ ለሀገሩ ባለው ፍቅር መሰረት በመሆኑ ውሳኔውም ለአሜሪካ የተሻለውን በማሰብ የተወሰነ ነው ብለዋል፡፡

ጆ ባይደን ሀገሩን ለዘመናት በትጋት ያገለገለ መሪ እንደሆነ በማንሳት ውሳኔውም ተገቢ ነው ያሉት ደግሞ የቼክ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር ፔትር ፊአላ ናቸው፡፡

የፖላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶናልድ ተስክ ፕሬዝዳንት ባይደን ዲሞክራሲን እና ነፃነትን የሚያጠናክሩ ከባድ ውሳኔዎችን ብዙ ጊዜ ወስነዋል፤ ይህ ራስን ከምርጫ የማግለል ውሳኔ ግን ለሀገር የተሻለውን ከመመኘት የተነሳ ነው ብለዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በቀጣዩ የአሜሪካ ምርጫ እንደማይሳተፉ ማሳወቃቸውን ተከትሎ የሀገራት መሪዎች መልዕክት እያስተላለፉ ይገኛሉ።

በሔለን ታደሰ