ፕሬዝዳንት ኤርዶጋን ለ10 ሀገራት አምባሳደሮች ማስጠንቀቂያ ሰጡ

ፕሬዝዳንት ኤርዶጋን

ጥቅምት 12/2014 (ዋልታ) የቱርክ ፕሬዝደንት ሪሴፕ ጣይብ ኤርዶጋን የአሜሪካ፣ ጀርመን እና ፈረንሳይን ጨምሮ የ10 ሀገራት አምባሳደሮችን ከሀገራቸው ሊያባርሩ እንደሚችሉ አስጠነቀቁ፡፡

ፕሬዝደንት ኤርዶጋን ማስጠንቀቂያውን የሰጡት በእስር ላይ የሚገኘው ኦስማን ካቫላ ከእስር እንዲለቀቅ የሚጠይቅ መግለጫ አምባሳደሮች ማውጣታቸውን ተከትሎ ነው።

ኦስማን ካቫላ እ.አ.አ በ2013 በኢስታንቡል ጌዚ ፓርክ ተካሂዶ የነበረውን ህዝባዊ አመፅ በመምራት ተከሶ ነው ተያዘው።

መግለጫው ያወጡት በቱርክ የአሜሪካ፣ ጀርመን፣ ካናዳ፣ ዴንማርክ፣ ኖርዌይ፣ ፊንላንድ፣ ፈረንሳይ፣ ስዊድን፣ ኒውዚላንድ እና ኔዘርላንድስ አምባሳደሮች ናቸው።

ድርጊቱ ያስቆጣቸው ፕሬዝደንት ኤርዶጋን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው አስሩንም አምባሳደሮች ጠርቶ እንዲያናግር በሰጡት ትዕዛዝ መሰረት ሚኒስትሩ አነጋግረዋቸዋል።

ኤርዶጋን በጉዳዩ ላይ በሰጡት መግለጫ “እነኚህን አስር አምባሳደሮች በሃገራችን የምናቆይበት ሁኔታ ሊኖር እንደማይገባ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትራችን ነግሬዋለሁ” ብለዋል።

ኤርዶጋን ኤንቲቪ ለተባለ ጣቢያ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ላይ የአምባሳደሮቹ ተግባር ፍፁም ከመርህ የወጣ እና ሉአላዊነትን የጣሰ መሆኑን አስገንዝበዋል። “እናንተ ናችሁ እንዴ እኛን የምታስተምሩት?” በማለትም ቁጣቸውን ገልፀዋል።

በእስር ላይ የሚገኘው ካቫላ የምዕራብ መንግስታት ሴራ ፈፃሚ እንደሆነ በተደጋጋሚ የሚገልፁት ፕሬዝዳንቱ፣ የሃገራቱም መግለጫ የዚሁ ማሳያ እንደሆነ ጠቁመዋል። “እናንተ በሃገራችሁ ወንበዴ፣ ገዳይን ወይ አሸባሪን ከእስር ትለቃላችሁ?” ሲሉም ጠይቀዋል።

ተጠርጣሪው ገለልተኛ በሆነ ችሎት እየተዳኘ መሆኑን ተናግረው፣ ይህን ጉዳይ አስታኮ የሚመጣ የምዕራብ አገራት ጫና ቦታ እንደሌላቸው አስምረዋል።