መስከረም 19/2014 (ዋልታ) ዘንድሮ እስከ ጥቅምት ወር መጨረሻ በህብረት ሥራ ማህበራት በኩል 1 ነጥብ 1 ሚሊየን ኩንታል የግብርና ምርቶችን ለማህበረሰቡ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን የፌዴራል ህብረት ሥራ ኤጀንሲ ገለጸ።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡስማን ሱሩር “አሸባሪው ህወሃት የውጊያ ግንባሩን ከጠመንጃ ውጊያ በተጨማሪ በመላው አገሪቱ የኢኮኖሚ አሻጥር በመፍጠር ድምፅ አልባ ጦርነት ከፍቷል” ብለዋል።
በተለይም በከተሞች አካባቢ የአሸባሪውን ቡድን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በሚደግፉ ኃይሎች የኑሮ ውድነት እንዲባባስ እየሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።
እነዚህ አካላት ከአሸባሪው ሕወሓት ተልእኮ በመቀበል ህብረተሰቡ በኑሮ ውድነት እንዲማረርና በመንግሥት ተስፋ እንዲቆርጥ ጥረት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
“ይህን ድምፅ አልባ ጦርነት ለማምከን የህብረት ሥራ ዘርፉ ሰፊ ሥራ ሲሰራ ቆይቷል” ያሉት አቶ ኡስማን፤ በዚህም ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።
ሁሉንም የሚጎዳውን ይህን ጅምላ ጨራሽ የሆነ የኢኮኖሚ አሻጥር ለመመከት አምራች የህብረት ሥራ ማህበራት የግብርና ምርቶችን አሰባስበው ከኢንዱስትሪና ከሸማች ማህበራት ጋር ቀጥታ የሆነ ትስስር እንዲፈጥሩ መደረጉን ገልጸዋል።
አምራቹ ላመረተው ምርት ፍትሃዊ ዋጋ እንዲያገኝ ሸማቹም የሚፈልገውን ምርት በተመቸው ቦታና ጊዜ በተመጣጣኝ ዋጋና ጥራት እንዲያገኝ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
ባለፉት ሁለት ወራት 253 ሺሕ ኩንታል ምርት ተዘጋጅቶ ለሸማችና ኢንዱስትሪ ማህበራት እንዲቀርብ መደረጉን ጠቅሰዋል።
“እስከ ጥቅምት ወር መጨረሻ ድረስ ደግሞ 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል የግብርና ምርቶችን ለማህበረሰቡ ለማቅረብ እየተሰራ ነው” ብለዋል።
የጤፍ፣ ስንዴ፣ በቆሎና የማሽላ ምርቶች የሚቀርቡ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከአትክልት ሽንኩርትና ቲማቲም፣ ከቅመማ ቅመም በርበሬ እንዲሁም ከጥራጥሬ ምስር፣ አተር፣ ሽምብራና ባቄላ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በአማራ፣ ሲዳማ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች እንደየአካባቢያቸው ሁኔታ ምርቶቹን ለማቅረብ የተለዩ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
በአዲስ አበባና በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች እነዚህን ምርቶች ለማዳረስ እየተሰራ መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ምርቶች በማህበራት መቅረባቸው የተፈጠረው የዋጋ ንረት ትክክለኛ እንዳልሆነ ህብረተሰቡ እንዲረዳ የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል።
የኢኮኖሚ አሻጥር የመመከት ሥራ ተከታታይነት ያለው ስራ የሚጠይቅ በመሆኑ አሸባሪ ቡድኑ እስኪደመሰስ ድረስ በዘላቂነት እንደሚተገበር አስረድተዋል።
አሸባሪው የሕወሓት ቡድን የከፈተውን ሁሉን አቀፍ ጦርነት ለመመከት ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣም ጠይቀዋል።