10ኛው ሀገር ዐቀፍ የቱሪዝም ምርምር ጉባኤ በሰመራ እየተካሄደ ነው

ግንቦት 13/2014 (ዋልታ) በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ 10ኛው ሀገር ዐቀፍ የቱሪዝም ምርምር ጉባኤ “ቱሪዝም ለሥራ እድል ፈጠራ” በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ነው።

ጉባኤው በይፋ መከፈቱን ያበሰሩት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ነቢያ መሀመድ ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፉ ያልተነካ እምቅ ሀብት ያላት ሀገር ብትሆንም ከዘርፉ ተገቢውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም አግኝታለች የሚለው ጉዳይ ዛሬም ያልተመለሰ ጥያቄ ነው ብለዋል።

ዘርፉን ለማሳደግ ከታሰበ ሥራ አጥ ወጣቶችን በማሳተፍ ከቱሪስት መነሻ እስከ መዳረሻ ድረስ ሴክተሩን እያገዙ ኢኮኖሚያዊ ጥያቄያቸው እንዲመለስ ማገዝ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በቱሪዝም ዘርፉ ወጣቶችን በማሰልጠን ዘርፉ ጠንካራ የኢኮኖሚ ምንጭ እንዲሆን የተለያዩ ስልጠናዎችን እየሰጠ ነውም ብለዋል።

በጉባኤው የኢኮ-ቱሪዝም ዘርፍ ባለሙያዎች፣ የአስጎብኚ ማኅበራት እና የዘርፉ ተመራማሪዎች እየተሳተፉ ሲሆን የመጀመሪያው ጥናትና ምርምር ሥራዎች በመቅረብ ላይ ይገኛል።

የምርምር ጉባኤው በቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢኒስቲትዩት፣ በሰመራ ዩኒቨርሲቲና በአፋር ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በጋራ የተዘጋጀ ነው።

ደረሰ አማረ (ከሰመራ)

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW