10ኛውን የጣና ፎረም ስኬታማ ለማድረግ በቂ ዝግጅት መደረጉን ሚኒስቴሩ ገለጸ

ጥቅምት 3/2015 (ዋልታ) 10ኛውን የጣና ከፍተኛ የሴክዩሪቲ ፎረም ስኬታማ ለማድረግ በቂ ዝግጅት መደረጉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ መለሰ አለም በሳምንታዊ መግለጫቸው ከነገ ጀምሮ በባህር ዳር ከተማ በሚካሄደው 10ኛው የጣና ፎረም ዝግጅት እና በአረንጓዴ ዲፕሎማሲ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ጉባኤው ከጥቅምት 4 እስከ 6 ቀን 2015 ዓ.ም በባህር ዳር ከተማ የሚካሄድ ሲሆን የ3 ሀገራት መሪዎች እንዲሁም የቀድሞ ርዕሳነ መንግስቶች በጉባዔው ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

ጉባኤው በአካል ሲካሄድ ከሁለት አመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን በስኬት እንዲጠናቀቅም ከባለድርሻ አካላት ጋር በቂ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።

የአረንጓዴ ዲፕሎማሲን በተመለከተ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በመቀናጀት እንደሚካሄድ ገልጸው ችግኝ ተከላው በስድስት የአፍሪካ ሀገራት ይካሄዳል ብለዋል።

ችግኝ ተከላው በደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን፣ ጅቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ሩዋንዳ እና በኬኒያ ይካሄዳል ብለዋል።

በተያያዘ መረጃ የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በ10ኛው የጣና ፎረም ላይ ለመሳተፍ ባሕርዳር ገብተዋል።

የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለን (ፒኤችዲ) ጨምሮ የክልሉ እና  የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች አቀባበል እንዳደረጉላቸው የአሚኮ መረጃ አመላክቷል።