10ኛው የህክምና ትምህርት ቤቶች መማክርት እየተካሄደ ነው

ግንቦት 4/2014 (ዋልታ) የጤና ሚኒስቴር ከሐረማያ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው 10ኛው የህክምና ትምህርት ቤቶች መማክርት በሀረር ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
የጤና ሚኒስትር ዲኤታ ሰሃረላ አብዱላሂ እንደተናገሩት በኢትዮጵያ በጤና ዘርፍ የሚገኙ አበረታች ተግባራት እየተከናወኑ ነው፡፡
በተለይም ለማኅበረሰቡ ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት ከማሟላት አንፃር የቅድመ እና የድህረ ምረቃ ትምህርት ጥራትን ማሻሻል፣ የስፔሻሊስት ሀኪሞችን በብዛትና በጥራት ለማፍራት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ በ19 ተቋማት ላይ በ22 የህክምና ስፔሻሊስት ስልጠና ዘርፎች ስርዓተ ትምህርት ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ መገባቱን ጠቁመዋል፡፡
ከህክምና ተቋማት ተመርቀው የሚወጡ ባለሙያዎችም ችግርን የሚፈቱ መሆን እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።
በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የጤናና ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አህመድ መሀመድ በበኩላቸው ዩኒቨርስቲ ኮሌጁ ከመማር ማስተማር ጎን ጎን ለአካባቢው ማኅበረሰብ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለመስጠት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
መድረኩም በህክምና ትምህርት ውስጥ ያሉ መልካም ተሞክሮዎችን ለማስፋትና ክፍተቶች ለመቅረፍ እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።
ለሁለት ቀናት በሚካሄደው መድረክ ከግልና ከመንግሥት የህክምና ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ኃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል።
ተስፋዬ ኃይሉ (ከሀረር)
ለፈጣን መረጃዎች፦
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!