100 በጎ ፈቃደኛ የጤና ባለሙያዎች ወደ አማራ ክልል አቀኑ

ጥር 22/2014 (ዋልታ) በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች የተለያዩ የሕክምና ድጋፎች ለመስጠት ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ በጎ ፍቃደኛ የጤና ባለሙያዎች ወደ አማራ ክልል አቅንተዋል።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የምረቃ ተማሪዎች ኅብረት አስተባባሪነት የተሰባሰቡት የሕክምና ባለሙያዎቹ ከጥር 22 እስከ 29 ቀን 2014 በአማራ ክልል የሕክምና ምርመራ፣ ሕክምና እና የምክር አገልግሎት ይሰጣሉ፤ መድኃኒትም ያቀርባሉ ተብሏል።
ሸዋሮቢት፣ ኮምቦልቻ፣ ደሴ፣ ሐይቅ፣ ባቲ፣ ኩታበር፣ ቆቦና ወልዲያ የበጎ ፍቃደኞቹ መዳረሻ ከተሞች መሆናቸውን የኢዜአ መረጃ አመልክቷል።
የበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ በኮምፓሽን ኢንተርናሽናልም አስተባባሪነት የሚሰጥ ሲሆን ሰን ራይዝ ዴቨሎፕመንት ኢትዮጵያም አጋር ድርጅት ነው።
በኢትዮጵያ የኮምፓሽን ኢንተርናሽናል ዳይሬክተር ፀኃይ ወጣ በጎ ፍቃደኞቹ በጦርነቱ ለተጎዱ የማኅበረሰብ ክፍሎች የሕክምና ድጋፍ ይሰጣሉ ብለዋል።
በተለይም ደግሞ በጦርነቱ ለሥነ-ልቦና ቀውስ ለተጋለጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች የምክርና የሥነ-ልቦና ድጋፍ ላይ ትኩረት አድርገው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
ከበጎ ፍቃደኞቹ የጤና ባለሙያ መካከል ማርቆስ ድጉማ ለተገዱት የማኅበረሰብ ክፍሎች ተገቢውን ድጋፍ ለመስጠት ዝግጅቶች ሲደረጉ መቆየቱን ጠቁሟል።
ለእነዚህ የማኅበረሰብ ክፍሎች ድጋፍ ማድረግ የተጎጂዎቹን ሥነ-ልቦናና የቀደመ ሕይወታቸው ለመመለስ ትልቅ መነሳሳት እንደሚፈጥርላቸው ገልጿል።
ሌላዋ የጤና ባለሙያ ቤተልሔም ጌታቸው በሰለጠነችበት የሙያ መስክ ሕክምና በመስጠትና ምርመራ በማካሄድ የበኩሏን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀቷን ተናግራለች።
በጎ ፍቃደኞቹ ሌሎች በጤና እና በሌሎችም የሙያ መስኮች ያሉ ወጣቶች ወደ ሥፍራው በማቅናት ሠብዓዊ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።