100 የከተማ አውቶቡሶች ግዥ ለመፈፀም እየተሰራ መሆኑ ተጠቆመ

ሰኔ 21/2013 (ዋልታ) – በዓለም ባንክ ድጋፍ የአንድ መቶ አውቶቡሶች ግዥ ለመፈፀም እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ፡፡

አውቶቡሶቹ ሙሉ በሙሉ በአውሮፓ ስታንዳርድ ተጠናቀው የሚገቡ እያንዳንዱ አውቶቡስ ከስድስት እስከ ስምንት ሚሊየን ብር ወጪ ተደርጎበት ግዥው የሚፈፀም ይሆናል ተብሏል፡፡

የአውቶቡሶቹ ግዥ ተፈፅሞ ሲጠናቀቅም ለአንበሳ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት የሚሰጡ መሆናቸውን ከአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

አውቶቡሶቹም የከተማዋን የትራንስፖርት አገልግሎት ለማሳለጥ እና አሁን የሚታየውን የአቅርቦት ችግር ለመቅረፍ የማይተካ ሚና ይኖራቸዋል ነው የተባለው፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ በከተማዋ ምቹ፣ አስተማማኝና ተደራሽ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት የብዙሃን ትራንስፖርትን ለማስፋፋት ርብርብ እያደረገ ይገኛል፡፡