የአብን ከፍተኛ አመራር ክርስቲያን ታደለ ወደ ግንባር ለመዝመት መወሰናቸውን አስታወቁ

ክርስቲያን ታደለ

ኅዳር 14/2014 (ዋልታ) በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢና የአብን ፖለቲካዊ ጉዳዮች ኃላፊ ክርስቲያን ታደለ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጥሪ ተከትለው ወደ ግንባር ለመዝመት መነሳታቸውን አስታውቀዋል።

ኃላፊው “ለአገር አንድነትና ለሕዝብ ደኅንነት የምንሰስተው ሕይወት የለምና እኛም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር እንዘምታለን፤ ሕዝቤ ሆይ ተከተል!” ሲሉም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአገር መሪ ደረጃ ወደ ግንባር ለመዝመት መነሳታቸው ታሪካዊ ውሳኔ እንደሆነም ገልፀዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ እና ጥሪ ኢትዮጵያውያንን ከዳር እስከ ዳር ያነሳሳ እና ሁሉም ከመሪው ጎን ተሰልፎ መስእዋትነት ለመክፈል ያነሳሳ እንደሆነም አቶ ክርስቲያን አመልክተዋል።

የኅልውና ዘመቻው የኢትዮጵያን አንድነት ለማስጠበቅ፣ ለክብር እና ለነፃነት የሚደረግ ጦርነት ነው ያሉት ኃላፊው የጠቅላይ ሚኒስትሩን ውሳኔ ከኢትዮጵያውያንም በተጨማሪ በርካታ አፍሪቃውያንንም የሚያነሳሳ ነው ብለዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ ሁሉም በነቂስ ተነስቷል፤ ጥሪው ከዚህ ቀደም ከነበረው በተሻለ መናበብ እና ቁርጠኝነት ሁሉም እንዲነሳ ያደረገ እና ለጠላትም ትልቅ ሽብርን የሚፈጥር እንደሆነም ነው የገለፁት።