ለአማራ እና አፋር ክልል በጦርነት ለወደሙ የትምህርት ተቋማት የመጽሐፍት ማሰባሰብ ተጀመረ

ታኅሣሥ 15/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ወጣቶች ማኅበር ከጃፋር መጽሐፍት መደብር እና ጎደኝነት ለመልካምነት የበጎነት ስብስብ ጋር በጋራ በመሆን በአማራ እና በአፋር ክልል በጦርነት ለወደሙ የትምህርት ተቋማት የመጽሐፍት ማሰባሰብ ስራን አስጀመሩ።
‹ስጦታችን ለፈረሰው ትምህርት ቤታችን› በሚል መሪ ሀሳብ የተጀመረው የመጀመሪያ ዙር ስራ እስከ ጥር 30 የሚቆይ ሲሆን ከጀማሪ ጀምሮ ለተለያዩ የትምህርት ክፍል የሚጠቅሙ አጋዥ መጽሐፍት፣ የልብ ወለድ እንዲሁም የስነ ልቦናና ሌሎች የትምህርት አጋዥ መሳሪያዎች ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ይሰበሰባል ተብሏል።
ለዚህ በጎ ተግባር አምባሳደር ሆነው የተመረጡት የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ አስራት ሀይሌ እና ደራሲ እና ጋዜጠኛ ዘነበ ወላ በአስተባባሪዎቹ የተዘጋጀላቸውን መጽሐፍት በማስረከብ ንቅናቄውን አስጀምረዋል።
የትምህርት ጉዳይ የሁሉም ጉዳይ ነው ያሉት አስተባባሪዋቹ በአማራ እና በአፋር ክልል በጦርነት ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው የተፈናቀሉ ተማሪዋች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ የሚደረገውን ጥረት የትምህርት ግብአትን በመሰብሰብ እንዲያግዙ ጠይቀዋል።
የበጎ ተግባሩን ለማገዝ የሚፈልጉ ዜጎችም በአዲስ አበባ በሚገኙ የመንግሥት እና የግል ትምህርት ቤቶች በተመረጡ የመጽሐፍት መደብሮች እና የገና በዓል ባዛር በሚዘጋጅባቸው ስፍራዎች በመሄድ መጽሐፍትን በመለገስ አሻራውን እንዲያሳርፉ ተጠይቋል።
በመሰረት ተስፋዬ