125ኛው የአድዋ ድል በዓል በጎንደር ከተማ እየተከበረ ነው

የካቲት 23/2013 (ዋልታ) – የአድዋ ድል በዓል በጎንደር በልዩ ልዩ ዝግጅቶች በመከበር ላይ ይገኛል፡፡

በበዓሉ አባት አርበኞች፣ ወጣቶች፣ ልዩ ልዩ የጸጥታ አባላትና ከተለያዩ የከተማዋ ክፍሎች የተወጣጡ ነዋሪዎች ታድመዋል።

መነሻውን አርበኞች አደባባይ አድርጎ በጃንተከል መስቀል አደባባይ በመከበር ላይ የሚገኘው በዓሉ የጀግኖች አርበኞች የአድዋ ዘማቾችን ገድል የሚዘክሩ ትርዒቶችና ጭፈራዎችም ቀርበዋል።

ጎራዴ፣ ጋሻና ጦር የያዙ አርበኞች፣ ፉከራና ቀረርቶ የሚያወርዱ ወጣቶች፣ የአባቶችን ገድል ለመዘከር የታደሙ ፈረሰኞች የበዓሉ ድምቀት መሆናቸውን አብመድ ዘግቧል።

በጎንደር ከተማ እየተከበረ የሚገኘው በዓሉ ትናንት የታሪክ መምህሩ ታየ ቦጋለን ጨምሮ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተወጣጡ ምሁራንና አርበኞች እንዲሁም ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የተወጣጡ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች በተገኙበት በፓናል ውይይት መከበሩ ይታወቃል።