13ኛው የፌደራልና የክልል ማረሚያ ቤት ኮሚሽነሮች የጋራ ጉባኤ እየተካሄደ ነው

ነሀሴ 21/2021 (ዋልታ) – 13ኛው የፌደራልና የክልል ማረሚያ ቤት ኮሚሽነሮች የጋራ ጉባኤ “በለውጥ መርህ በተቃኘ አስተሳሰብ የህግ ታራሚዎችን የሰብአዊ መብት አያያዝ፣ የማረምና ማነጽ አገልግሎት ወደ ላቀ ደረጃ እናደርሳለን” በሚል መሪ ሀሳብ በባቱ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

የፌደራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል ዳመነ ዳሮታ ወደ ማረሚያ ቤቶች የሚላኩ ዜጎች ሠብአዊና ህገ-መንግስታዊ መብቶቻቸው ተጠብቆ እንደሚያዙ ገልጸው በቆይታቸውም የቀለም ትምህርትና የልዩ ልዩ ሙያ ባለቤት እንዲሆኑ ከምን ጊዜውም በተሻለ ሁኔታ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ማረሚያ ቤቶች ዜጎች የሚታፈኑበት፣ ግፍና ሰቆቃ የሚደርስባቸው ቦታዎች ሳይሆኑ ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ ባስቀመጠው መሠረት ታርመውና ታንፀው፣ አምራችና ህግ አክባሪ ሆነው ወደ ሠላማዊ ህይወት የሚመለሱባቸው ተቋማት መሆናቸውን ገልፀዋል።

የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ ዋና አቃቢ ዶክተር ጌድዮን ጢሞቲዎስ በበኩላቸው በኢትዮጵያ  ከሚገኙ የፍትህ ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው የፌደራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን በሪፎርም ውስጥ ተጨባጭ ለውጥ ከመጣባቸው ተቋማት መካከል አንዱና ዋነኛው ነው ብለዋል፡፡

ማረሚያ ቤቶች አሁን ከሚገኙበት ደረጃ ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ግን የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ርብርብ የሚጠይቅ ተግባር መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ተቋሙ የማረምና ማነፅ ስራውን ከተጨባጭ ወቅታዊ የሃገሪቱ ሁኔታ እንዲሁም ከዘመናዊ የማረሚያ ቤት የአሠራር ስርዓቶች፣ ቴክኖሎጂዎችና መሠረተ-ልማቶች ጋር እያጣጣመና እያዘመነ መሄድ ይገባዋል ነው ያሉት፡፡

በዓመት ሁለት ግዜ የሚካሄደው ይህ ጉባኤ ለሁለት ቀናት የሚቀጥል ይሆናል፡፡

በጉባኤው የ12ኛው ጉባዔ ቃለ ጉባኤ መርምሮ ማጽደቅ፣ የፌዴራልና የክልል ማረሚያ ተቋማት ሪፎርም አፈጻጸም የሚገኝበት ደረጃ መገምገም፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እና የወደፊት አቅጣጫዎች የሚመላከቱበት ይሆናል፡፡

በተጨማሪም በሃገራዊ ማረሚያ ቤቶች ፀጥታና ደህንነትና ሌሎች ተጨማሪ አጭር መነሻ እቅድ ቀርቦ ውይይት ተካሄዶበት እንደሚጸድቅ ይጠበቃል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ ጠቅላይ አቃቢ ህግ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ፣ የፌደራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል ዳመነ ዳሮታ እንዲሁም የፌዴራልና የክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ኮሚሽነሮች ተገኝተዋል።

(በዙፋን አምባቸው)