13 ኢትዮጵያውያን በጀልባ መስጠም አደጋ ሕይወታቸው አለፈ

ነሐሴ 20/2016 (አዲስ ዋልታ) በየመን የባሕር ዳርቻ አካባቢ በደረሰ የጀልባ መስጠም አደጋ 13 ኢትዮጵያውያን መሞታቸውን የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኤጀንሲ አስታውቋል።

14 ሰዎች ደብዛቸው የጠፋ ሲሆን የነፍስ አድን ሰራተኞች የማፈላለግ ሥራ እየሰሩ መሆኑ ተገልጿል።

የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይ ኦ ኤም) 25 ኢትዮጵያውያን እና ሁለት የመናዊያንን አሳፍራ ከጅቡቲ የተነሳች የስደተኞች ጀልባ መስጠሟን አስታውቋል።

ምክንያቱ እስካሁን ባልታወቀው የጀልባዋ መስጠም አደጋ ከሞቱት መካከል 11 ወንዶች ሲሆኑ ሁለቱ ደግሞ ሴቶች ናቸው።

በየመን የአይ ኦ ኤም ኃላፊ ማት ሁበር “ይህ አሳዛኝ አደጋ ስደተኞች በዚህ መስመር ላይ የሚያጋጥሟቸውን አደጋዎች አጉልቶ ያሳያል፤ ይህ የስደት መስመር ከመቼውም በላይ አስከፊ አደጋ ያለበት እና በሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎች የተሞላ በመሆኑ የዜጎችን ሞት ለመቀነስ የሁሉም ጥረት አስፈላጊ ነው” ብለዋል።

ከፈረንጆቹ 2014 ጀምሮ በዚህ ቀጣና ብቻ 6 መቶ 93 በባሕር ላይ የሰጠሙ ሰዎችን ጨምሮ 2 ሺሕ 82 የስደተኞች ሞት ተመዝግቧል።

በየመን ያለው አለመረጋጋት እየጨመረ ቢሄድም ከዚህ በተቃራኒ ዜጎች በሕገ ወጥ መንገድ ወደዚህ ስፍራ የሚያደርጉት ጉዞ እየተበራከተ መምጣቱን የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት መረጃ ያመላክታል።