14 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት በመላው ሀገሪቱ ሊሰራጭ መሆኑ ተገለጸ

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)

 

ሐምሌ 28/2016 (አዲስ ዋልታ) 14 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት ግዥ ተፈጽሞ በመላው ሀገሪቱ ለማሰራጨት በዝግጅት ላይ መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለፁ።

በሚኒስትሩ የተመራ የፌዴራልና የክልል የንግድ ሴክተር የሥራ ኃላፊዎች በአዳማ ጉምሩክ ቅርንጫፍ በመገኘት ከውጭ እየገባ ያለውን የፍጆታ እቃዎች ተመልክተዋል።

በአዳማ ጉምሩክ ቅርንጫፍና በሌሎች ቅርንጫፎች የፍጆታ ዕቃዎችን ጭነው የቆሙ ከ1ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎች ምርቱን ዛሬና ነገ ወደ ገበያ የማስገባት ስራ እንደሚጀምሩ ገልጸዋል፡፡

በዚህም የገበያን ፍላጎት ከመሙላት ባለፈ የመሰረታዊ ሸቀጦች አቅርቦት እጥረት እንዳይኖር ለማድረግ 14 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት ግዥ ተፈፅሞ ወደ ሀገር ውስጥ እየገባ ይገኛል ብለዋል።

የምግብ ዘይት ምርቱ በማከማቻ መጋዘኖች ሳይራገፍ ቀጥታ ወደ ክልሎች ለማጓጓዝ የሚያስችል መዋቅር መዘርጋቱንም ነው የተጠቀሰው፡፡

የንግዱ ማህበረሰብ የተሟላ ግንዛቤ እንዲኖረውና የተፈጠረውን የግንዛቤ ክፍተት ለመሙላት የሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የንግድ ቢሮዎችና የግብርና ሴክተሮች ትምህርታዊ ግንዛቤ እየሰጡ እንደሚገኙም አክለዋል ።

በመሆኑም ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ የታየባቸው የብረት፣ ሲሚንቶ፣ ቆርቆሮና ሌሎች የግንባታ ዕቃዎችን ጨምሮ የፍጆታ ምርቶች ከውጭ ምንዛሪ ተመን ማሻሻያና ከማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ፕሮግራም ይፋዊ ትግበራ በፊት በነበረው ዋጋ መቀጠል እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡

በምንም መልኩ ዋጋ ለመጨመር የሚያበቃ ምክንያት ያለመኖሩን የገለጹት ሚኒስትሩ ህገወጥ ነጋዴዎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና አስካሁን 2ሺህ 20 ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል፡፡

ከማሸግ ባለፈም የንግድ ፍቃዳቸውን መሰረዝና ከንግዱ መስመር እንዲወጡ የማድረግ ስራ በዘላቂነት እንደሚሰራ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡