14 ኮሌጆች በመጪው እሁድ ከ6 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ያስመርቃሉ

የካቲት 03/2013 ዓ.ም አዲስ አበባ (ዋልታ)፣ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ 14 የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኮሌጆች በመጪው እሁድ ከ6 ሺህ በላይ ተማሪዎችን እንደሚያስመርቁ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡

የአስተዳደሩ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ንጋቱ ዳኛቸው ለኢዜአ እንደጠቆሙት፤ በከተማዋ የሚገኙ ስድስት የፖሊቴክኒክ ኮሌጆችና ስምንት የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጆች ተማሪዎቻቸውን ያስመርቃሉ።

በመጪው እሁድ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ በሚካሄደው የምረቃ ስነ-ስርዓት ኮሌጆቹ በ11 የተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ከሁለት እስከ አራት ዓመት ያሰለጠኗቸውን 6 ሺህ 800 ተማሪዎች እንደሚያስመርቁ ነው ያስታወቁት።

ተማሪዎቹ ከሰለጠኑባቸው የሙያ መስኮች መካከል ኮንስትራክሽን፣ ጨርቃጨርቅ፣ አውቶሞቲቭ እና አይሲቲ የትምህርት ዘርፎች ይገኙበታል።

ባለፈው ዓመት መመረቅ የነበረባቸው ተማሪዎች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሳቢያ ቢዘገዩም የማካካሻ ሥልጠና ወስደው በአሁኑ ወቅት ለምረቃ መዘጋጀታቸውን አቶ ንጋቱ አብራርተዋል፡፡