1442ኛው የኢድ አል አደሃ በዓል በደሴና ወልድያ እየተከበረ ነው

ሐምሌ 13/2013 (ዋልታ) – 1 ሺህ 442ኛው የኢድ አል አደሃ አረፋ በዓል በደሴ እና ወልድያ ከተሞች እየተከበረ ይገኛል፡፡

የደሴ ከተማ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ከማለዳ ጀምሮ በተክቢራና በሌሎችም ሃይማኖታዊ ክንውኖች በዓሉን እያከበሩ ሲሆን፥ በፉርቃን መስጅድ የኢድ ሶላት አድርሰዋል፡፡

ሕዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር የተቸገሩትን በመርዳትና የተፈናቀሉ ወገኖቹን በመጠየቅ ሊሆን እንደሚገባ የሃይማኖቱ ተከታዮች ገልጸዋል፡፡

የህዳሴ ግድቡ ሁለተኛ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት በመከናወኑም ደስታ እንደተሰማቸው የበዓሉ ተሳታፊዎች የገለጹ ሲሆን፥ በቀጣይም ለሀገር ሰላም በጋራ ልንቆም ይገባል ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ የአረፋ በዓል በወልድያ ከተማ እየተከበረ ሲሆን፥ የዳዕዋና የበዓሉን አስተምህሮ ለምዕመኑ ያብራሩት ኡስታዝ አብደላ መሐመድ ለሚስኪኖች እንዘን የድርሻቸውንም እንስጥ ብለዋል፡፡

ኡስታዝ መሐመድ አሕመዲን እንዳሉት፥ በሰላም ጉዳይ መደራደር የለብንም፤ ሰላም ከሌለ ኢድ የለም፤ ለሰላማችን እንፀልይ፣ ለሰላም አንትጋ ብለዋል ሲል አሚኮ ዘግቧል፡፡

እዚህ ስንሰግድ ከጀርባችን የሚጠብቁን ልዩ ኃይሎች እና የሀገር መከላከያ ተክቢራና ዱዓ ያስፈልጋቸዋል፥ ለደኅንነታችን ስለሚሞቱም ደጀን ልንሆናቸው ይገባል ነው ያሉት፡፡

በዓሉ ሚስኪኖችን በመርዳት፣ ተፈናቃዮችን በመዘየር በደም ልገሳ እየተከበረ ነው፡፡