1442ኛው የኢድ አል አደሃ በዓል በባህርዳር ከተማ እየተከበረ ነው

ሐምሌ 13/2013 (ዋልታ) – 1ሺህ 442ኛው የኢድ አል አድሃ በዓል በባሕር ዳር ከተማ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሁነቶች እየተከበረ ይገኛል፡፡

በበዓሉ የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሰይድ ሙሐመድን ጨምሮ የሃይማኖት አባቶች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና የእምነቱ ተከታዮች ተገኝተዋል፡፡

ሼህ ሰይድ ሙሐመድ በመልዕክቸው፣ በዓሉን ስናከብር የተቸገሩትን በመርዳት፣ የተራቡትን በማብላት እና በማጠጣት ኀላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል፡፡

ማንኛውም አቅም ያለው የእስልምና እምነት ተከታይ በሕይዎት ዘመኑ አንድ ጊዜ ሐጂ በሚፈጸምበት ቦታ በመሄድ የሐጂ ስርዓት መፈጸም እንዳለበት ከአምላክ የተሰጠ ትእዛዝ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ሼህ ሰይድ የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል እስማኤል ለአባቱ ለኢብራሂም እና ለአምላኩ ለአላህ ታዛዥነቱን ያሳየበት በዓል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በኢድ አል አድሃ በዓል የሃይማኖቱ ተከታዮች በየዓመቱ ዘር ቀለም ቋንቋ ሳይገድባቸው ከአራቱም የዓለም ጫፍ ተገናኝተው የሚያከብሩት መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

ሼህ ሰይድ ይህንን ታሳቢ በማድረግ በሀገራችን በተፈጠሩ ችግሮች ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ሰዎች ድጋፍ ማድረግ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡

“የዚህን ዓመት በዓል ስናከብር በርካታ ሀገራዊ ድሎችን ያስመዘገብንበት ዓመት በመሆኑ ደስታችን እጥፍ ነው፤ ይህ ደስታችን እንዲቀጥል ሁላችንም ኀላፊነታችንን ልንወጣ ይገባልም ነው ያሉት፡፡

ፕሬዚዳንቱ ሀገር ወደ ተሻለ ጉዞ እንድታቀና ሁሉም በገንዘብ በጉልበት እና በሀሳብ በማገዝ ኀላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፣ በተለያየ ችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን በጸሎት ማሰብ እንደሚገባም መልእክት ማስተላለፋቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡