15ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በብሔራዊ ትያትር አዳራሽ ተከበረ

የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማቱ 15ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በዓልን በብሔራዊ ትያትር አዳራሽ “እኩልነትና ህብረ- ብሔራዊ አንድነት ለጋራ ብልጽግና” በሚል መሪ ቃል አከበሩ፡፡

የበዓሉን የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው እንደገለጹት የዘንድሮው በዓል ከሌላው ለየት የሚያደርገው ህብረ ብሔራዊነታችንን የምናደምቅበት እና ከመቼውም በተለየ ሁላችንም ለጋራ ብልጽግና የምንጓዝበት መንገድ ላይ በመሆናችን ብለዋል፡፡

ሚኒስትሯ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን አከባበር ሲታሰብ ልዩነት ብቻ ሳይሆን በውስጡ በአንድነት የሚታይ ውበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዓሉ የብሔራዊ ትያትር የባህል ቡድን የብሔር ብሔረሰብ ባህላዊ ሙዚቃ በማቅረብ ለበዓሉ ድምቀት መስጠቱ ተጠቅሷል፡፡

ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ሃብታሙ ሲሳይ በበኩላቸው የብሔር ብሔረሰቦች በዓል አከባበር ጋር ተያይዞ ከህገ መንግስቱና ከወቅታዊ ጉዳዮች ጋር አዛምደው የስፖርት ዘርፍ የውይይት ሰነድ አቅርበው ውይይት እንደተካሄደበት ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡