16ኛው የአፍሪካ ወጣቶች ቀን በአርባ ምንጭ ተከበረ

16ኛው የአፍሪካ ወጣቶች ቀን

ኅዳር 1/2015 (ዋልታ) የአፍሪካ ወጣቶች ቀን “የወጣቶች ንቁ ተሳትፎና ተካታችነት ለስብዕና ልማት” በሚል መሪ ቃል በኢትዮጵያ ለ16ኛ ጊዜ በአርባ ምንጭ ከተማ ተከበረ፡፡

የዘንድሮው የአፍሪካ ወጣቶች ቀን አፍሪካዊያን ችግራቸውን በራሳቸው መንገድ መፍታት እንደሚችሉ የፌዴራል መንግስት ከህወሓት ጋር ባደረገው የሰላም ስምምነት ኢትዮጵያ ምሳሌ መሆኗን ያስመሰከረችበት በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል ሲሉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

የአፍሪካ ወጣቶች ቀን መከበር ዋና ዓላማው የአኅጉሪቱ ወጣቶች እርስ በርስ ተቀራርበው በአፍሪካ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊና ፖለቲካዊ ጉዳዩች ዙሪያ በመወያየት አፍሪካን በሁሉም መስክ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ትኩረት ያደረገ መሆኑን ሚኒስትሯ አብራርተዋል፡፡

ትምህርት ዓለምን የሚለውጥ መሳሪያ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ወጣቶች የለውጥ ኃይል፣ የአዳዲስ ሀሳብ አፍላቂዎች እና የአንድ ሀገር የጀርባ አጥንት መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በሀገሪቱ ያሉ ወጣቶች አቅማቸውን ሙሉ በሙሉ ለልማት ማዋል ከቻሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ የመጣውን የኑሮ ውድነት በመግታት ኢትዮጵያን ከድህነት ሰንኮፍ ማላቀቀ እንደሚቻል ሚኒስትሩ አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡

ሀገር የጀመረችውን የልማትና የእድገት ጎዳና ከታለመለት ዓላማ ለማድረስ እና የተረጋገጠ ሰላም ለማስፈን የወጣቶች ሚና ከፍተኛ መሆን እንዳለበት የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዳምጠው ዳርዛ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

በተለይም ኢትዮጵያን ካደጉት ሀገራት ተርታ ማሰለፍ የሚቻለው ጊዜን በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል ሲቻል ነው ሲሉም አክለዋል፡፡

አመለወርቅ መኳንንት (ከአርባምንጭ)