2ኛው የኢትዮ-ቻይና የጋራ ፖለቲካዊ ምክክር ተካሄደ

መጋቢት 7/2014 (ዋልታ) ሁለተኛው የኢትዮ-ቻይና የጋራ ፖለቲካዊ ምክክር በዛሬው ዕለት ተካሂዷል።

በቴሌ ኮንፈረንስ አማካኝነት በተካሄደው ምክክር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና የቻይና ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴንግ ሊ ተሳትፈዋል።

ሁለቱ አገራት በጋራ ቀጣናዊና ዓለም ዐቀፍ ጉዳዮች ላይ የተወያዩ ሲሆን ስትራቴጂካዊ ግንኙነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።

ሁለቱ ወገኖች የአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ እና የመንገድ ልማት፣ የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር አስተዳደርና ጥገና እንዲሁም በኮቪድ-19 የኢትዮ-ቻይና ትብብርን ጨምሮ በተለያዩ ምጣኔ ሃብታዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

የትሕነግ ፀብ አጫሪ እንቅስቃሴዎች ቀጥለው ባሉበት ሁኔታ የኢትዮጵያ መንግሥት ሰላምን ለማረጋገጥ የወሰዳቸውን እርምጃዎች አምባሳደር ሬድዋን ማብራራታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል።

ረዳት ሚኒስትር ዴንግ ሊ በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግሥት ሰላምን ለማረጋገጥ የወሰዳቸውን እርምጃዎች አድንቀው የቻይና መንግሥት ችግሩ በውይይት እንዲፈታ ያለውን ፍላጎት አንፀባርቀዋል።