ሐምሌ 14/2013 (ዋልታ) – 2ኛው ዙር የህዳሴ ግድብ ውሃ ሙሊት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና የሚያረጋግጥ የለውጡ ትሩፋት ነው ሲሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ገለጹ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ ይህን ያሉት የሲዳማ ክልል ህዝብ ሁለተኛው ዙር የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሊት በስኬት በመጠናቀቁ ደስታውን ለመግለጽ ባካሄደው ሰልፍ ላይ በተገኙበት ወቅት ነው።
ግድቡን ለማሰናከል ጠላቶች ብዙ ቢደክሙም የሙሌት ሥራውን ከማከናወን ሊያስቆሙን አልቻሉም፤ ወደፊትም አያስቆሙንም ብለዋል።
ለግድቡ ከኢትዮጵያውያን የተዋጣውን ገንዘብ ሕወሓት በመዝረፍ ሀገራችንን የማዳከም ሥራ ሲሰራ ቆይቷል ያሉት አቶ ደስታ ሌዳሞ፣ ይህንና ሌሎችም ሀገር አጥፊ ተልዕኮዎቹን አጥብቀን እንቃወማለን ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ከልማታችን የሚያስቆመን አንዳችም ሀይል እይኖርም፤ ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድረስ ሙሉ ድጋፍ እናደርጋለን ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ጁንታውን እንቃወማለን፣ ከመከላከያችን ጎን በመቆም የሀገራችንን ዳር ድንበር እናስከብራለን ሲሉም ለሰልፉ ለታዳሚዎች ገልጸዋል።
2ኛው ዙር ሙሊት በስኬት በመጠናቀቁ ለክልሉ ህዝብ የእኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ በበኩላቸው፣ ይህም የአንድነታችን ውጤት ነው ብለዋል።
አሁንም አንድነታችንን አጠናክረን ኢትዮጵያን ከጠላቶቿ እንጠብቅ ሲሉም ጥሪ ማቅረባቸውን ደሬቴድ ዘግቧል።