2ኛው ዙር የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት የሶስቱ አገራት ብሄራዊ ገለልተኛ የሳይንቲስቶች ቡድን ባዘጋጀው የውሃ ሙሌት መርሃ ግብር መሰረት እንደሚካሄድ ተገለጸ

ግንቦት 14/2013 (ዋልታ) – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በኦታዋ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ኤምባሲ እና ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ጥምረት በካናዳ በጋራ ባዘጋጁት የዌቢናር ስብሰባ ላይ የህዳሴ ግድብን አስመልክተው መልዕክት አስተላልፈዋል።
አቶ ደመቀ ባስተላለፉት በዚሁ መልዕክት ኢትዮጵያ የዜጎቿን የኃይል ችግር ለመቅረፍና የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የውሃ ሀብቷን መጠቀም ግዴታዋ በመሆኑ፣ ይኸው ተግባር የታችኞቹን የተፋሰስ አገራት በማይጎዳ መልኩ እንደሚካሄድ ጠቅሰዋል።
አያይዘውም ኢትዮጵያ ለናይል ወንዝ 86 በመቶ የሚሆነውን ውሃ የምታበረክት እንደመሆኗ መጠን በዚሁ አግባብ የህዳሴ ግድብ ግንባታን መጀመሯን አስታውሰዋል፡፡
ከግድቡ ጋር ተያይዞ በግብጽና በሱዳን በኩል የሚነሱ ስጋቶችን ለመቅረፍ እ.ኤ.አ በ2015 በሶስቱ አገራት መካከል በተፈረመው የመርሆዎች መግለጫ ስምምነት መሰረት ውይይቶች መካሄዳቸውን ጠቅሰው፤ መፍትሔ ባልተደረሰባቸው ጉዳዮች ላይም በአፍሪካ ህብረት አስተባባሪነት ተከታታይ ድርድሮች መደረጋቸውን አብራርተዋል።
ግድቡ በታችኞቹ የተፋሰሱ አገራት ላይ የጎላ ጉዳት እንደማያመጣ የሚታወቅ ቢሆንም በሱዳን እና በግብጽ በኩል ግን ጉዳዩን ዓለም አቀፍ መልክ እንዲይዝ በማድረጋቸው በአፍሪካ ህብረት አስተባባሪነት የሚካሄደውን ድርድር እያደናቀፉ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሁለቱም አገራት የናይል ወንዝ ውሃን በጋራ እና በፍትሃዊነት ከመጠቀም ይልቅ የቅኝ ገዥዎችን ስምምነት ለማጽናት ያላቸው ፍላጎት ለድርድሩ ሂደት ተግዳሮት እንደሆነም አስረድተዋል፡፡
አሁንም በአፍሪካ ህብረት አስተባባሪነት የሚደረገወው የሶስትዮሽ ድርድር በውሃ ሙሌት እና አስተዳደር ላይ አተኩሮ እንዲቀጥል የኢትዮጵያ ፍላጎት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ግብጽና ሱዳን ኢትዮጵያ ስምምነት ባለመፈረሟ የድርድር ሂደቱን እንዳስተጓጎለች ተደርጎ የሚቀርበው ክስ መሠረት ቢስ መሆኑን ገልጸው፤ አጠቃላይ የውሃ ሀብት ክፍፍልን የሚመለከቱ ጉዳዮች ሁሉንም የናይል ተፋሰስ አገራት የሚመለከት ጉዳይ እንደሆነ አብራርተዋል።
ሁለቱ አገራት ኢትዮጵያ ወደ ፊት ውሃ የመጠቀም መብቷን የሚገድብ አስገዳጅ ውል እንድትገባ የሚያደርጉት ግፊት ተገቢነት እንደሌለውም አስረድተዋል፡፡
በመሆኑም የውሃ ሙሌቱ በመርሆዎች ስምምነት መሰረት የግንባታው አካል በመሆኑ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት የሶስቱ አገራት ብሄራዊ ገለልተኛ የሳይንትስቶች ቡድን ባቀረበው የውሃ አሞላል መርሃ ግብር ስምምነት መሰረት በተያዘለት ጊዜ እንደሚከናወን አቶ ደመቀ አረጋግጠዋል፡፡
በካናዳ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ናሲሴ ጫላ በበኩላቸው ግድቡን በተመለከተ በሚድያዎች የሚተላለፉ የተዛቡ መረጃዎችን ለማረም፣ የግድቡ ድርድር ያለበትን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ግልጽነት ለመፍጠር እና ሁሉንም ወገን ተጠቃሚ የሚያደርግ ስምምነት ለመድረስ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን አስመልክቶ መድረኩ በቂ ግንዛቤ እንደሚፈጥር ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
የግድቡን ቴክኒካዊ ጉዳይ በተመለከተ ፕሮፌሰር ይልማ ስለሽ፤ እንዲሁም የድርድሩን ይዘትና በየአገራቱ የሚነሱ ልዩነቶችን በተመለከተ ወ/ት ለምለም ፍስሃ ለተሳታፊዎቹ የውይይት መነሻ ጽሁፍ ማቅረባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡