2ኛው ዙር የኢድ እስከ ኢድ ዝግጅት ስኬት ባለድርሻ አካላት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ

2ኛው ዙር የኢድ እስከ ኢድ ዝግጅት

ግንቦት 9/2014 (ዋልታ) ሁለኛው ዙር የኢድ እስከ ኢድ ዝግጅት የኢትዮጵያን ገፅታ ይበልጥ ለማስተዋወቅ በሚያስችል ደረጃ እንዲዘጋጅ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ።

ከኢድ እስከ ኢድ ክብረ በዓል የመርኃ ግብሮች አፈፃፀም፣ የእስካሁን ሥራዎች እና ቀጣይ ተግባራትን የገመገመ ውይይት ብሔራዊ ፈፃሚ ኮሚቴው ትላንት በበይነ መረብ አከናውኗል።

በውይይቱ እስካሁን ሲደረግ የነበረው የመጀመሪያው ዙር መርኃ ግብር በአብዛኛው በታቀደው መሰረት እየተፈፀመ መሆኑ ተመልክቷል።

የብሔራዊ ፈፃሚ ኮሚቴው ጣምራ ሰብሳቢና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በሀገር ውስጥ ተቋማት መካከል እንዲሁም ከሚሲዮኖች ጋር በጥሩ ቅንጅት በመስራት የመጀመሪያውን ዙር ከኢድ እስከ ኢድ ክብረ በዓል በስኬት ማከናወን ተችሏል ብለዋል።

የተገኘው ተሞክሮም የሁለተኛው ዙር ሥራዎችን በላቀ ሁኔታ ለማከናወን እገዛ እንደሚኖረውም አመልክተዋል።

የብሔራዊ ኮሚቴው ጣምራ ሰብሳቢ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ በመጀመሪያው ዙር የኢድ እስከ ኢድ አከባበር ሃይማኖታዊ ይዘቱን የጠበቀ፣ ሕዝብን በነቂስ ያሳተፈ እና የሃገርን ገፅታ ያስተዋወቀ እንደነበር ተናግረዋል።

ከመርኃ ግብሮቹ አንዱ የሆነውን ታላቁ የኢድ ሶላትን ለማወክ የተሞከረው እንቅስቃሴ የከፋ ጉዳት ሳያስከትል መቆጣጠር መቻሉን በማስታወስ ለዚህም የፀጥታ አካላትን አመስግነዋል።

በቀጣይ መርኃ ግብር የተያዙ ታላላቅ ሃይማኖታዊ እና ሕዝባዊ መርኃ ግብሮች እንዳሉም ጠቁመዋል።

ሁለተኛው ዙር ከኢድ እስከ ኢድ ዝግጅት ሰኔ 24 ቀን 2014ዓ.ም እንደሚጀምር በውይይቱ የተገለፀ ሲሆን ሕዝብን አሳታፊ የሆኑ መርኃ ግብሮች መታቀዳቸውም ታውቋል።

አንዳንድ ተቋማት ላይ በመጀመሪያው ዙር የታየው ኃላፊነትን በሚጠበቀው መጠን ያለመወጣት ክፍተት በሁለኛው ዙር እንዲታረም ተጠይቋል።

ሁለተኛው ዙር መርኃ ግብር በተሻለ የተቋማት ቅንጅት እና ቅድመ ዝግጅት የሀገሪቱን ገፅታ ይበልጥ ማጉላት በሚያስችል መልኩ ለመፈፀም እንዲሰራም ነው የኮሚቴው ጣምራ ሰብሳቢ ጥሪ ማቅረባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።