2ኛ ዙር የመሰረታዊ ውትድርና ስልጠና በሁርሶ ተጀመረ

ሚያዚያ 29/2013 (ዋልታ) – የ2013 ዓ.ም ለሁለተኛ ዙር የመሰረታዊ ውትድርና ሰልጣኞች የስልጠና ማስጀመሪያ መርሀ-ግብር በሁርሶ ኮንቲጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ተካሄደ፡፡

የተገኙት የትምህርት ቤቱ ዋና አዛዥ ኮሎኔል አዲሱ ተርፋሳ የውትድርና ሙያ ለሀገር ያለንን ፍቅር እስከ ህይወት መስዋትነት ለመክፈል በፍላጎት እና በሙሉ ፍቃደኝነት ወደ ሰራዊት የምንቀላቀልበት ሙያ ነው ብለዋል፡፡

ሽብርተኛው ህወሓት በሰሜን ዕዝ ሰራዊታችን ላይ የፈፀመው አፀያፊ የክህደት ተግባር በህግ ማስከበር ዘመቻው የጁንታውን ሀይል በመደምሰስ ሀገር የማዳኑን ስራ በጀግንነት በፈፀምንበት ማግስት የታሪኩ ተቋዳሽ በመሆናችሁ ልትኮሩ ይገባል ብለዋል ኮሎኔል አዲሱ ተርፋሳ፡፡

የመሰረታዊ ውትድርና ለመሰልጠን የተቀላቀሉ ሁሉ ከጥንት ጀምሮ አባቶች በመስዋትነት ያቆዩዋትን ሀገር የማስቀጠል ሀላፊነትን በማሰብ ስልጠናውን በአግባቡ መውሰድ እንደሚገባ አስታውሰዋል፡፡

ሰልጣኞቹ በሚኖራቸው ቆይታ ብቁ ወታደር ለመሆን የሚያስችላቸውን እውቀት እና ክህሎት እንደሚያዳብሩ ከየኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡