የካቲት 16/2013 (ዋልታ) – ባለፉት ስድስት ወራት 1,988,214,981 ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የገቢና ወጪ ኮንትሮባንድ ዕቃዎች መያዙንየገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ከዚህ ውስጥ 1,608,582,897 ብር የሚገመቱ የገቢ ኮንትሮባንድ እቃዎችና ህገ-ወጥ ገንዘብ ሲሆን 379,632,084 ብር የሚገመቱ የኮንትሮባንድ እቃዎችና ህገ-ወጥ ገንዘብ ከሃገር ሊወጡ ሲሉ መያዛቸውንም ጠቁመዋል ፡፡
የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ የተያዙት በ14 ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ሲሆን ሀዋሳ፣ ጅግጅጋ እና ድሬዳዋ የሚገኙ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ከፍተኛ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የገቢ ኮንትሮባንድ ዕቃዎች በቁጥጥር ስር እንዲውል በማድረግ ቀዳሚውን ስፍራ ሲይዙ የወጪ ኮንትሮባንድ እቃዎች ሞያሌ፣ አዲስ አበባ ኤርፖርትና ሀዋሳ ከፍተኛ ዋጋ ያለው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች የተያዙ መሆናቸውንም አብራርተዋል፡፡
ከሀገር ሊወጡ ሲሉ የተያዙት ኮንትሮባንድ ዕቃዎች ዓይነት አደንዛኝ እፆች፣ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር እና ማዕድናት ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ ሲይዙ ወደ ሀገር በመግባት ላይ እያሉ የተደረሰባቸው ዋና የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ተሽከርካሪዎች፣ አዳዲስ አልባሳት እና ኤሌክትሮኒክስ መሆናቸውንም ገልፀዋል፡፡
የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹን በመያዝ የተሳተፉ የጉምሩክ አመራርና ሰራተኞች እንዲሁም በየደረጃው የሚገኙ የጸጥታ አካላት ልባዊ ምስጋናችውን አቅርበው የኮንትሮባንድ ንግድን ለመከላከል የገቢዎች ሚኒስቴርና የጉምሩክ ኮሚሽን ከሚሰሩት በተጓዳኝ የሁሉም ዜጋ ተሳትፎና ቁርጠኝነት ወሳኝ መሆኑን አንስተው ሁላችንም የድርሻችን ልንወጣ ይገባል ሲል ሚኒስቴሩ ጥሪ አቅርቧል፡፡