22.5 ቢሊየን ብር ግምት ያለው ብረት በአገር ውስጥ መመረቱ ተገለጸ

ግንቦት 25 ቀን 2013 (ዋልታ) በበጀት ዓመቱ በ10 ወራት ጊዜ ውስጥ 22 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ግምት ያለው ብረታ ብረት በአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች መመረቱን የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ገለጸ።

በሀገሪቱ የብረታ ብረት ኢንዱስትሪዎች ያለባቸውን ችግር በመፍታት የምርት ፍላጎቱን በራስ አቅም ለመሸፈን እየተሰራ መሆኑም ተነግሯል።

ኢንስቲትዩቱ በብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ የማምረት አቅም ለማሳደግና ያሉበትን ማነቆዎች ለመፍታት የሚያግዝ የምክክር  መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተካሂዷል።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ አስፋው ረጋሣ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ በዓመት 10 ነጥብ 9 ሚሊዮን ቶን የማምረት አቅም ያላቸው የሀገር ውስጥ የብረታ ብረት ማምረቻ ኢንዱስትሪዎች  ከአቅም በታች እያመረቱ ነው።

ኢንዱስትሪዎቹ የኢትዮጵያን የብረታ ብረት ምርት ፍላጎት የመሸፈን አቅም እንዳላቸው ተናግረዋል።

“ሆኖም ግን የግብዓት አቅርቦትና የውጭ ምንዛሪ እጥረት ማነቆ በመሆኑ እያመረቱ ያሉት በሚፈለገው ደረጃ አይደለም” ብለዋል።

በኢንስቲትዩቱ የእቅድ፣ ፖሊስ ጥናትና መረጃ  ዳይሬክተር አቶ ጥላሁን አባይ በበኩላቸው በሀገሪቱ የብረታ ብረት ፍላጎትን ለማሟላት የሚያስችል አቅም እንዳለ ጠቅሰዋል።

በብረታ ብረት ዘርፍ የተሰማሩ ኢንዱስትሪዎች በሙሉ አቅማቸው ቢያመርቱ ከሀገር ውስጥ ፍላጎት  አልፈው የውጭ ምንዛሬ ማምጣት እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

የሀገር ውስጥ የብረታ ብረት ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን የጠቀሱት አቶ ጥላሁን፤ “ባለፉት አስር ወራት 22 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ግምት ያለው ብረታ ብረት ተመርቷል” ብለዋል።

ኢንዱስትሪዎቹ እያጋጠሟቸውን ችግሮች ለመፍታት ዘርፉ ከሚመለከታቸው 16 ተቋማት ጋር የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ባለፉት አስር ዓመታት ከ89 ቢሊዮን ዶላር በላይ በማውጣት ለብረታ ብረት ግዥ መዋሉን ጠቅሰዋል።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዮሐንስ ድንቃየሁ የሀገሪቱ የብረታ ብረት ኢንዱስትሪዎች የአቅማቸውን 15 በመቶ ብቻ እያመረቱ እንደሆነ አብራርተዋል።

ይህንን ችግር ለመፍታት ከፌዴራል መንግስት ጀምሮ በየደረጃው ያለው መዋቅር ዘርፉን እንዲደግፉ ለማስቻል ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ሚኒስትር ዴኤታው አስረድተዋል።