የአውሮፓ ህብረት ለሲቪል ማህበራት ከ3 ነጥብ 7 ሚሊየን ዩሮ በላይ ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19/2008(ዋኢማ)-የአውሮፓ ህብረት የሲቪል ማህበረሰብ ፈንድ በኢትዮጵያ ለ44 የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ከ3 ነጥብ 7 ሚሊየን ዩሮ በላይ ድጋፍ አደረገ።

ድጋፉ የተደረገው በመልካም አስተዳደር፣ በሴቶች ተሳትፎ፣ በሰብዓዊ መብት፣ በንግድ፣ በግብርና፣ በትምህርትና ሌሎችም ማህበራዊ አገልግሎቶች ለሚሰሩ ድርጅቶች ነው።

በኢትዮጵያ የአውሮፓ የህብረት ተወካይ ምክትል ሃላፊ ተርሂ ሌቲነን እንዳሉት፥ ድጋፉ የተደረገላቸው ተቋማት ለማህበረሰቡ በተለያየ መልኩ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች ናቸው።

ከገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ ህብረቱ የአቅም ግንባታና የማማከር አገልግሎት እንደሚሰጥም አረጋግጠዋል።

ህብረቱ በመጀመሪያው ምዕራፍ (ከ2006 እስከ 2016) በኢትዮጵያ ለ250 ሲቪል ማህበራትና መንግስታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች የ14 ነጥብ 9 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ አድርጓል።

እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር እስከ 2019 በሚዘልቀው የሁለተኛው ምዕራፍም የ3 ነጥብ 755 ሚሊየን ዩሮ ድጋፉን በዛሬው እለት ይፋ አድርጓል።

በሶስተኛው ምዕራፍም አጠቃላይ የ16 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ ለመስጠት አቅዷል።

በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት ሲቪል ማህበረሰብ ፈንድ የቴክኒካል ድጋፍ ጽህፈት ቤት ቡድን መሪ አቶ አካለወልድ ባንቲርጉ፥ ድጋፉ የተፈቀደላቸው ድርጅቶች የማወዳደሪያ መስፈርት ወጥቶ ማለፍ የቻሉት ናቸው ብለዋል።

በውድድሩም በአገሪቷ ፖሊሲና ስትራቴጂ መሰረት በመንግስት ያልተደረሱ ክፍተቶችን የመሸፈን አቅምና ፍላጎቱ ያላቸው ድርጅቶች ተለይተው ለድጋፉ መመረጣቸውን አስረድተዋል።

ድርጅቶቹ የተረደገላቸውን ድጋፍ በአግባቡ ስራ ላይ ማዋላቸውን ለመከታተል እንዲቻል በቀጣይ ከክልል መንግስታት ጋር ስምምነት እንደሚፈራረሙ ይጠበቃል።(ኢዜአ)