በከተማዋ ከ7ሺ500 በላይ የመስሪያ ቦታዎች ተሰጡ

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ ለተሰማሩ ከ7500 በላይ አንቀሳቃሾች የመስሪያ ቦታ ተጥቷል ተባለ፡፡

በከተማዋ ለ10ሺ አንቀሳቃሾች የመስሪያ ቦታ ለማስተላለፍ ታቅዶ እንደነበር በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመስሪያ ቦታዎች ልማትና አስተዳደር ኤጄንሲ ለዋልታ ገልጿል፡፡ በዚህም የዕቅዱን 75 በመቶ አሳክቷል፡፡

ኤጄንሲው ቀደም ሲል የነበረውን አሰራር በተጠናከረና ግልፅነትን በተከተለ መልኩ ለማስኬድ የመስሪያ ቦታዎችን ለማልማት፤ለማስተላለፍና ለማስተዳደር መቋቋሙን የኤጄንሲው ኃላፊ አቶ ግዴና ኃ/ሥላሴ ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ሁሉም በዘርፉ የሚሰማሩ አካላት መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በፍትሃዊነትና በግልፅነት የመስሪያ ቦታዎችን እንዲያገኙ ኤጄንሲው በትኩረት እየሰራ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ቀደም ሲል ግንባታቸው ከተጀመሩ 66 ፕሮጀክቶች የ44ቱ መጠናቀቁን ኃላፊው አስረድተዋል፡፡ ቀሪዎቹም ቶሎ ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ ተገቢው ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ ነው፡፡ ግንባታቸው ተጠናቆ መሰረተ ልማት ያልተሟላላቸው 193 የመስሪያ ቦታዎችም አስፈላጊው መሰረተ ልማት እንዲሟላላቸው መደረጉን ጨምረው ገልፀዋል-አቶ ግዴና፡፡

ከህግ አግባብ ውጭ ተይዘው የነበሩ ከ127 በላይ የመስሪያ ቦታዎችንም በማስለቀቅ ለሚመለከታቸው አካላት ማስተላለፋቸውን ኃላፊው አስረድተዋል፡፡

ኤጄንሲው የመስሪያ ቦታ አቅርቦትና ዝግጅትን በማሳለጥ በዘርፉ የሚነሱ ቅሩታዎችን ለመፍታት ራሱን በሰው ኃይልና በግብዓት እያጠናከረ መሆኑን አቶ ግዴና ተናግረዋል፡፡

የመስሪያ ቦታዎች ለአንቀሳቃሾች ምቹና ለሚሰማሩበት ዘርፍ ተገቢ በሆኑ አካባቢዎች የመገንባት አሰራርን እንደሚከተሉ ኃላፊው ይናገራሉ፡፡ ለዚህም ተገቢው ጥናትና ዝግጅት ተደርጎ ወደ ሥራ ይገባል ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በከተማዋ በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ የተሰማሩ አንቀሳቃሾችና የተፈጠረውን የሥራ ዕድል በጠራ መልኩ ለማወቅ ከገለልተኛ ወገን በተውጣጣ ቡድን ጥናት እየተካሄደ ነው፡፡ በቅርቡም ይፋ ይደረጋል ብለዋል፡፡