ኢትዮጵያ በሶስት አካባቢዎች የፀሃይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ለሚያከናውኑ የውጭ ኩባንያዎች ጨረታ አውጥታ እያወዳደረች ነው።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጅነር አዜብ አስናቀ እንዳሉት፥ ሑመራ፣ መተሃራና መቐለ 100 ሜጋ ዋት የፀሃይ ሃይል ይመነጭባቸዋል ተብለው የተለዩ አካባቢዎች ናቸው።
ፕሮጀክቱን ለሚያከናውኑ የግል ኩባንያዎች ጨረታ ወጥቶ ውድድሩ እየተጠናቀቀ መሆኑንም ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም በዘርፉ ልማት ለመሳተፍ የሚመጡ የውጭ ሃገር ኩባንያዎች ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ የመግባቢያ ሰነድ እየተፈረመ ፍላጎት ያላቸው ይወዳደሩ እንደነበር ጠቅሰው፥ ፍላጎት ያላቸው ኩባንያዎች ቁጥር በመጨመሩ ጨረታ በማውጣት እንዲወዳደሩ እየተደረገ ነው ብለዋል።
እንደ ኢንጂነር አዜብ ገለፃ፥ በአሁኑ ጨረታ 75 የውጭ ሃገር ኩባንያዎች ተሳትፈዋል።
የኩባንያዎቹ መረጣ የሚካሄደው የለማውን ኃይል በተሻለ ወይም በአነስተኛ ዋጋ ሊያቀርብ የሚችል፣ ኃይል አምርቶ የመሸጥ ልምድ፣ የሥራ አፈፃፀም ልምድና በመሰል መስፈርቶች መሆኑን ተናግረዋል።
የውል ስምምነት ሲደረግ ኩባንያዎቹ የሚያመርቱትን ኃይል መንግስት የሚገዛቸው ይሆናል።
የሃገሪቷ የኢነርጂ ዘርፍ ፖሊሲ ባለሃብቶች የኤሌክትሪክ ሃይል ማልማት እንዲችሉ የሚፈቅድ ሲሆን፥ 50 በመቶ ያህሉ በግል አልሚዎች እንዲለማ ስትራቴጂ ተነድፏል።
በሃገሪቷ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅምን በ2012 ዓ.ም 17 ሺህ 208 ሜጋ ዋት ለማድረስ ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።( ኤፍቢሲ)