በበጀት ዓመቱ ከ18 ሺህ በላይ የ40/60 ቤቶች ለተጠቃሚዎች ይተላለፋሉ

የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር በበጀት ዓመቱ 18 ሺህ 496 40/60 ፕሮግራም ቤቶችን እንደሚያስተላልፍ ገለጸ። 

የሚኒስቴሩ ሠራተኞች በመስሪያ ቤቱ 2009 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ተወያይተዋል።

ሚኒስቴሩ በበጀት ዓመቱ ቀደም ሲል ግንባታቸው የተጀመሩ 37 ሺህ 498 40/60 እና 132 ሺህ 702 20/80 ፕሮግራም ቤቶችን አፈጻጸም 45 በመቶ ለማድረስም አቅዷል።

በግንባታ አፈጻጸም ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ በሚፈጥሩ ርዕሰጉዳዮች ዙሪያም ስድስት ጥናቶችን ያከናውናል።

የከተማ ቤቶች መረጃ አስተዳደርን ለማጎልበትም በበጀት ዓመቱ 200 ሺህ የመንግስትና የጋራ ህንፃ ቤቶች መረጃ ይሰበሰባል።

ሚኒስትር መኩሪያ ኃይሌ በውይይቱ ወቅት "የህብረተሰቡን ችግር ከመፍታት አኳያ በጊዜ የለንም መንፈስ ልንሰራቸው የሚገቡ ብዙ ስራዎች አሉ" ነው ያሉት።

ሚኒስቴሩ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በቤት አቅርቦት ለባለሃብቶችና ለሌሎች መሰረተ ልማቶች መሬት በማቅረብ ረገድ ጉልህ ድርሻ አለው ብለዋል።

የከተማ አስተዳደሮችና የክልል መንግስታት እነዚህን ጉዳዮች በፍጥነት እንዲሄዱባቸው ሚኒስቴሩ የበኩሉን ድርሻ ይጫወታል ብለዋል።

በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች 1 ሺህ 126 ሄክታር የለማ መሬት፣ 1 ሺህ 782 ሼድ፣ 72 ህንጻና ሶስት የገበያ ማዕከላት ግንባታ መከናወኑን በክትትልና ድጋፍ በማረጋገጥ ግብረ መልስ ይሰጣል ተብሏል።(ኢዜአ)