ኢትዮጵያውያን ለህዳሴ ግድባቸው ከ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ አስተዋፅኦ አድርገዋል

መላው ህዝብ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በተለያየ መልኩ እያደረገ ያለው ድጋፍ ሁለገብ በሆነ መልኩ መቀጠሉን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ገለፀ።

የጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ገብረስላሴ እንደተናገሩት፥ ባለፉት አምስት አመታት በተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሮች አማካኝነት ከ8 ነጥብ 7 ቢልየን ብር በላይ ለግድቡ ግንባታ ተሰብስቧል።

ከህዝቡ የሚሰበሰበው የገንዘብ መጠንም በየአመቱ ከፍተኛ ጭማሪ እያሳየ መሆኑን የሚያነሱት ዋና ዳይሬክተሯ፥ ሊጠናቀቅ ቀናት በቀሩት የ2008 አመተ ምህረት ብቻም ህብረተሰቡ ከ1 ነጥብ 2 ቢልየን ብር በላይ በተለያየ መንገድ ለግድቡ ግንባታ አስተዋፅኦ አድርጓል።

በ8100 “A” አጭር የጽሁፍ መልዕክት በ2007 እና 2008 በሁለት ዙሮች 180 ሚሊየን ብር የተገኘ ሲሆን፥ ከሎተሪ 49 ሚልየን ብር፣ ከተለያዩ የሙዚቃ ስራዎች ፣ ከስፖርትና ከህብር የሙዚቃ አልበም በጋራ ደግሞ ከ134 ሚልየን ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል።

ህብረተሰቡ በጽህፈት ቤቱ እና በየሚሠራበት ተቋም በኩል ግድቡ ድረስ እየሄደ ጉብኝት ማድረጉ እና ሲመለሱ ግድቡ ያለበትን ሁኔታ ለሌሎች በማሳወቅ ህዝቡ የባለቤትነት ስሜቱን እንዲያጠናክርና ድጋፉንም እንዲቀጥል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉ ለዚህ ውጤት መገኘት ምክንያት ሆነዋል።

በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያ ክልል እየተዘዋወረ የሚገኘው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋንጫም ከፍተኛ ገቢን ያስገኘ ሲሆን፥ ከ800 ሚልየን ብር በላይ ተሰብስቦበታል።

ዋንጫው በእስካሁኑ የኦሮሚያ ክልል ቆይታውም 250 ሚልየን ብር ገቢ ያስገኘ ሲሆን፥ ወደ ቀጣይ ክልል እስከሚሄድ ድረስ የሚያስገኘው ገቢ 500 ሚልየን እንደሚደርስ ይጠበቃል።

በአዲሱ አመትም ይህን ህዝባዊ ተሳትፎ በአዳዲስ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሮች አጠናክሮ ለማስቀጠል እቅድ መያዙን ነው ጽህፈት ቤቱ የገለፀው።

ወይዘሮ ሮማን እንዳሉት፥ የተለያዩ ዝግጅቶችን በማዘጋጀት ብሄራዊ መግባባቱ ተጠናክሮ የማስቀጠል፣ ግድቡ ያለበትን ሁኔታ ግልጽ የማድረግ እና የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራዎች ይከናወናሉ። (ኤፍ.ቢ.ሲ)