ከ386 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የሐረር ከተማ ተለዋጭ አስፋልት መንገድ ተጠናቀቀ

የመጀመሪያው የአምስት ዓመት የእድገትና የትራስፎርሜሽን ዕቅድ የመንገድ ዘርፍ ልማት ኘሮግራም አካል የሆነው በታሪካዊነቷ የምትታወቀውን የሐረር ከተማ አቋርጦ የሚያልፈው ዋና የአስፋልት መንገድ ግንባታ መጠናቀቁን የባለሥልጣኑ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት አስታወቀ፡፡

አቶ ሳሙሶን ወንድሙ እንደገለጹት 20 ኪ.ሜ ርዝመት የሚሸፍነው የዚህ መንገድ ግንባታ የትራፊክ መጨናነቅን ለማቃለል አዲስ አቅጣጫን በመከተል ስፋትና ደረጃውን እንዲጠብቅ ታስቦ የተሰራ መንገድ ሲሆን፣ የትራፊክ ፍሰቱን የተቀላጠፈ እንደሚያደርገው ታምኖበታል፡፡ በአስፋልት ኮንከሪት ደረጃ የተገነባው ይህ መንገድ የመንገድ ትከሻን ጨምሮ 10 ሜትር ስፋት እንዲኖረው ተደርጎ የተገነባ ነው፡፡ 

ከ386 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የመንገዱን ግንባታ ያከናወነው ገምሹ በየነ አገር በቀል የሥራ ተራጭ ድርጅት ሲሆን፣ የማማከርና የቁጥጥር ሥራውን ያከናወነው ኮር ኮንሰልቲንግ የተባለው ሃገር በቀል አማካሪ ድርጅት ነው፡፡ 

የመንገዱ ግንባታ የተጀመረው በሚያዝያ 2006 ዓ.ም ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ግንባታው ተጠናቆ ለትራፊክ ክፍት ሆናôል፡፡ ለመንገድ ኘሮጀክቱ ማስፈፀሚያ የዋለው ብር አጠቃላይ ወጪ የተሸፈነው በኢትዮጵያ መንግሥት በጀት ነው፡፡

የሐረር ከተማ ተለዋጭ አስፋልት ኮንከሪት መንገድ ከመሐል ሃገር ተነስቶ ኦሮሚያን እና ሐረርን የሶማሊያ ብ/ክልል ርዕሰ ከተማ ከሆነችው ከጅጅጋ ከተማ ጋር በቀጥታ የሚያገናኝ ሲሆን፣ በመስመሩ ላይ የሰፈሩትን አርሶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች ሁለገብ ጠቀሜታ ያሳድጋል ተብሎ ይታመናል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በቱሪስት መስህብነት የምትታወቀውን የሐረር ከተማ ለመጎብኘት የሚመጡ ቱሪስቶች እንደልብ እንዲንቀሳቀሱ ከማስቻሉም በላይ ለአካባቢ ልማት እና የገበያ ትስስር ለመፍጠር ትልቅ ሚና ይጫወታል፡፡