ክልሉ ለሥራ አጥ ወጣቶች የእርሻ መሬት አቀረበ

 የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በ10 ማህበራት ለተደራጁ ሥራ አጥ ወጣቶች ከ40 ሄክታር በላይ መሬት ማቅረቡን አስታወቀ፡፡ በመሬቱ ላይ ለማልማት እንዲችሉም ገንዘብ በብድር የሚያገኙበት ዕድል እንደሚመቻችም ነው የተገለፀው፡፡

በክልሉ ሥራ አጥ ወጣቶችን በማህበር በማደራጀት በግብርና ዘርፍ እንዲሰማሩ በማድረግ የሥራ ዕድል እየተፈጠረ መሆኑን የክልሉ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሀብታሙ ታዬ ለዋልታ ተናግረዋል፡፡ እያንዳንዱ ማህበርም አንዳንድ ትራክተር እንዳለው አስረድተዋል፡፡

በንብ ማነብ፣በአነስተኛ መስኖ ልማት፣ በብረታ ብረት ሥራ ዘርፍ በክልሉ ከፍተኛ የሥራ ዕድል እንዳለ ኃላፊው ጠቁመው ከዚህም በተጨማሪ ሥራ አጥ ወጣቶች በሌሎች  የሥራ ዘርፎች  የሚሰማሩበትን ዕድል ለመፍጠር እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በ2009 ዓ.ም በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ለወጣቶች በርካታ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር ታቅዶ እየተሰራ እንደሆነም አቶ ሀብታሙ ተናግረዋል፡፡

አቶ ሀብታሙ እንዳሉት በክልሉ ነዋሪዎችን በመንደር የማሰባሰብ መርሀ ግብር በ2003 ዓ.ም ተጀምሯል፡፡ ይህም በተለያየ ቦታ ተበታትነው የነበሩ ነዋሪዎች በአንድ ቦታ እንዲሰባሰቡ ረድቷል፡፡ ውሃና ሌሎች የተለያዩ መሰረተ ልማቶችንም በአቅራቢያቸው ለማግኘት ችለዋል፡፡

ክልሉ ወጣቶችን በማህበራት በማደራጀት የሥራ ዕድል በመፍጠር ሀብት የሚያፈሩበትን መንገድ ለማመቻት ማገዘዙንም ነው ኃላፊው የተናገሩት፡፡

በምዕራብ ኢትዮጵያ የሚገኘው የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በለም መሬትና በተለያዩ የተፈጥሮ ሀብቶች  የታደለ ነው፡፡ ለአገሪቱ አግሮ ኢንዱስትሪ ልማትም ትልቅ አስተዋፅዖ ያበረክታል፡፡

በግብርናው ዘርፍ የሚሰማሩ ባለሀብቶች በክልሉ ተሰማርተው በማልማት የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም ነው ከክልሉ የተገኘው መረጃ የሚያስረዳው፡፡

መንግስት የሥራ ዕድል ፈጠራን በማሳደግ ወጣቶች ሀብት በማፍራት ራሳቸውንና አገራቸውን እንዲጠቅሙ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡