የሕዝቦችን ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማረጋጋጥ የተለያዩ ሥራዎች ተከናውነዋል -ምሁራን

ባለፉት 15 ዓመታት የአገሪቱ ሕዝቦች ከአገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገቱ ፍትሃዊ ተጠቃሚ  እንዲሆኑ ለማስቻል የተለያዩ ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን  ምሁራን ገለጹ ።

በብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዶክተር አብርሃ ተከስተ ለዋኢማ እንደገለጹት ባለፉት 15 ዓመታት ግብርና መር ኢኮኖሚን ተግባራዊ በማድረግ 77 በመቶ የሚሆነውን    የገጠር ህዝብ በግብርና እንዲሁም በከተሞች ኢኮኖሚያዊ ለውጥ በማምጣት ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።

በአገሪቱ የሚገኙ ሴቶችና ወጣቶች በተለያዩ ዘርፎች ተደራጅተው የራሳቸውን ሥራ እየፈጠሩ መሆናቸውን የጠቆሙት ዶክተር አብርሃ በአገሪቱ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ኢኮኖሚውን ይበልጥ እንዲያነቃቁት በማድረግ በኩል ግን ብዙ የሚቀሩ ሥራዎች እንዳሉ ገልጸዋል ።

በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ የኢኮኖሚክስ መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ተሾመ አዱኛ በበኩላቸው በአንድ አገር ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማምጣት መንግሥት ለኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት ሰፊ ትኩረት መሥጠት አለበት በማለት ባለፉት 15 ዓመታት ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት ለኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አገልግሎቶች መስፋፋት ተገቢውን ትኩረት ሠጥቶ ሲሰራ መቆየቱን አስታውቀዋል ።

በአንድ አገር የኢኮኖሚ  እንቅስቃሴ ውስጥ  ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉት በኢኮኖሚ ውስጥ  ንቁ ተሳታፊ የሆኑ ዜጎች  ብቻ  ሊሆኑ እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡

በአገሪቱ  ተወዳዳሪነትን ፣ እውቀትን፣ ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረገና የግል ዘርፉን ያቀፈ ጠንካራ ኢኮኖሚን መገንባት ለሁሉም ለዜጎች ፍትሃዊ የሆነ ኢኮኖሚን ለመፍጠር ያግዛል ብለዋል ረዳት ፕሮፌሰር ተሾመ ።

በአገሪቱ በተከታታይ ከተመዘገበው የኢኮኖሚ ዕድገትና ልማት መላ የአገሪቱ ብሔር ፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን ከማውጣት ጀምሮ ልማቱን ተግባራዊ ለማድረግ ልዩ ልዩ ጥረቶች ሲካሄዱ ቆይተዋል ።