ዓለም አቀፉ የግሎባሊክ ኩባንያ በኢትዮጵያ የኃይል ልማት የመሳተፍ ፍላጎት እንዳለው ገለፀ

ዓለም አቀፉ የግሎባሊክ ኩባንያ በኢትዮጵያ የኃይል ልማት ዘርፍ የመሳተፍ ፍላጎት እንዳለው አስታወቀ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም የኩባንያውን የምስራቅ አፍሪካ ተወካይ ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

የኩባንያው ተወካይ ክርስትን ራይት በኢትዮጵያ እያደገ ያለውን የኃይል ልማት ፍላጎት ለማሟላት ኩባንያው ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት እንዳለው መግለጻቸውን ውይይቱን የተከታተሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ተወልደ ሙሉጌታ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በተለይም በጂኦተርማልና በፀሃይ ኃይል የሚለማ ከፍተኛ ሃብት እንዳላት በመጥቀስ ኩባንያው ይህን ሃብት ጥቅም ላይ ለማዋል ይሰራል ብለዋል።

ኩባንያው በአፍሪካ ታላላቅ የኃይል ማመንጫዎችን በመገንባት ከፍተኛ ልምድ እንዳለውና በተለይም በኬንያና ታንዛኒያ ሰፊ ስራ መስራቱን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ከዕድገቷ ጋር ተመጣጣኝ ኃይል እንዲኖራት ኩባንያው ዓለም አቀፍ እውቅና ባላቸው ባለሙያዎች የታገዘ ስራ የመስራት ፍላጎት እንዳለውም አስታውቀዋል።

በመተሃራ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ስራ መሳተፍ የሚያስችለውን እንቅስቃሴ መጀመሩንም ተናግረዋል።

ዶክተር ቴድሮስ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በኃይል ልማቱ ዘርፍ ለምታከናውነው ስራ ድጋፍ እንደምትሻና ለዚህም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ ገልጸዋል።

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መንግስት ለኢንዱስትሪው ልማት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ በመሆኑ ኩባንያው ይህን ጥረት ያግዛል ብለዋል።

ኩባንያው በእንግሊዝና ኖርዌይ ባለሃብቶች የተቋቋመ ሲሆን ከአፍሪካ አገራት በኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ጋና፣ ደቡብ አፍሪካና ሌሎች አገራት በኃይል ልማት ዘርፍ ይሰራል።