836 ሜትር ታክሲዎች ታሪፍ ወጥቶላቸው በቀጣዩ ሳምንት አገልግሎት መሥጠት ይጀምራሉ

በአዲስ አበባ ወደ ሀገር ውስጥ የገቡት ሜትር ታክሲዎች ታሪፍ እና ታርጋ ቁጥር ወጥቶላቸው ከአንድ ሳምንት በኋላ ወደ አገልግሎት  ይገባሉ ተባለ።

ታክሲዎቹን የመመረቅ ሥነ ስርአት ዛሬ ጠዋት በመስቀል አደባባይ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በተገኙበት ተካሂዷል።

በስነስርአቱ ላይ የትራንስፖርት ሚኒስትሩ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ፥ ሜትር ታክሲዎቹ ለመዲናዋ ነዋሪዎች የአዲስ አመት ስጦታዎች ናቸው ብለዋል።

ታክሲዎቹ በከተማዋ የሚስተዋለውን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ ከፍተኛ ድርሻ እንደሚኖራቸውም ነው የተናገሩት።

በቀጣይ 500 አውቶብሶች  ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚገቡ የገለጹት ዶክተር ወርቅነህ፥ ሚኒስቴሩ በአዲሱ አመት 2009 የመዲናዋን የትራንስፖርት እጥረት ለመቅረፍ ይሰራል ብለዋል።

የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን እንደገለፀው 26 አክሲዮን ማህበራት እና ሶስት የግል ኩባንያዎች ተቋቁመው 1 ሺህ 163 ታክሲዎች ከቀረጥ ነፃ ወደ ሀገር ውስጥ እየገቡ ነው።

ከእነዚህ መካከል እስካሁን 836ቱ ሀገር ውስጥ መግባታቸውን ነው የባለስልጣኑ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ይግዛው ዳኛው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የተናገሩት።

ታክሲዎቹ በአለም አቀፍ ደረጃ ተሳፋሪው የሚሄድበትን ኪሎ ሜትር ልክ በማየት ክፍያ እንዲፈፅም የሚደረግባቸው ናቸው።

ባለስልጣኑ የታሪፍ መጠኑን እየሰራ ሲሆን ስምሪታቸውም ከፍተኛ የትራንስፖርት እጥረት በሚታይባቸው አካባቢዎች ይሆናል ተብሏል።

የታሪፍ መጠኑ ከተጠናቀቀ በኋላም በቀጣዩ ሳምንት ለከተማዋ ነዋሪዎች አገልግሎት መስጠት ይጀምራሉ።

ታክሲዎቹ ተሳፋሪዎች በተጓዙበት ርቀት ልክ ክፍያ የሚጠየቅባቸው ስለሚሆኑ፥ ከዚህ ቀደም ከላዳ ታክሲ ሾፌሮች ጋር ይደረግ የነበረውን ክርክር እና ግጭትን ያስቀራሉ ተብሎ ይጠበቃል።(ኤፍቢሲ)