ደብረብርሃንን ከአዋሽ አርባ የሚያገናኘው ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ተጀመረ

የኢትዮጵያ መንግስት በመደበው ከ1ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ በጀት ከደብረ ብርሃን -አዋሽ አርባ አቋራጭ 93 ኪሎ ሜትር መንገድ ግንባታ መጀመሩን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት አስታወቀ ፡፡

የባለስልጣኑ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት እንደገለጹት የደብረብርሃን – አንኮበር – አዋሽ አርባ መገንጠያ የመንገድ አንኮበር – ዱለቻ 40 ኪሎ ሜትር አስፋልት ኮንክሪት መንገድ ፕሮጀክት ግንባታ መጀመሩን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ ገልጸዋል ፡፡

የአፋርና የአማራ ክልሎችን የሚያስተሳስረው የአንኮበር -ዱለቻ መንገድ ግንባታ ጨረታውን በ858 ሚሊየን 761ሺ 475 ብር በማሸነፍ ግንባታውን የሚያከናውነው ሀገር በቀሉ ተቋራጭ ሰንሻይን ኮንስትራክሽን  ነው፡፡

መንገዱ ደረጃውን የጠበቀ የመንገድ አውታር ያልነበረው ሲሆን መስመሩ ካለው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አንፃር ወደ አስፋልት ኮንክሪት የሚያድግ ይሆናል ብለዋል ፡፡

ከደብረብርሃን ከተማ 40 ኪሎሜትር ርቀት አንኮበር ላይ ግንባታው የተጀመረው የአንኮበር-  ዱለቻ መንገድ የጎን ስፋት በገጠር 10 ሜትር በከተማ ደግሞ 14 ሜትር ሲሆን ፤በሁለት አመት ተኩል ውስጥ የመንገዱ ስራ እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል ፡፡

የመንገዱ አጠቃላይ አቀማመጥ ገደላማ እና ተራራማ ቦታ ላይ ያረፈ ሲሆን ግንባታው የሶስት አዳዲስ ድልድዮች ግንባታ እና ብዛት ያላቸው የውሃ መፋሰሻ ትቦ እና ቦይ ስራዎችን ማካተቱን አብራርተዋል ፡፡

ህዝቡን ዘመናዊ የመንገድ ትራንስፖርት ተጠቃሚ በማድረግ ስፍራው የሚታወቅበትን የቅባትና የግብርና ምርት ወደ መሃል ሀገር በመላክ ኢኮኖሚያቸውን በእጅጉ እንደሚያሳድግ አስረድተዋል ፡፡

መንገዱ ከባድ ተሸከርካሪዎችን ከጅቡቲ ወደብ ወደ ደብረብርሃንና አካባቢው ለመጓዝ ቢፈልጉ በአዲስ አበባ በኩል መዞር ሳያስፈልጋቸው በቀጥታ በአዋሽ አርባ -ደብረብርሃን ከተማ ሊገቡ እንደሚችሉ አመልክተዋል፡፡

በዚሁም ከዚህ ቀደም በነባሩ መንገድ ይፈጅ የነበረውን ረጅም ጉዞ የሚያሳጥር ከመሆኑም በላይ የጉዞ ግዜንና የተሸከርካሪ መጠቀምያ ወጪን በመቀነስ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አብራርተዋል ፡፡

ሌላው የዱለቻ- አዋሽ አርባ መገንጠያ 53 ኪሎ ሜትር መንገድ በብር 693 ሚሊየን 519 ሺ 819 ብር የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ጨረታውን በማሸነፍ በቅርቡ ወደ ግንባታ ስራው እንደሚገባ የሚጠበቅ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

መንገዱ በሶስት አመት ውስጥ የሚጠናቀቅ ሲሆን በአከባቢው የሚገኙ የመስተዳድር አካላትና ሕበረተሰብ መንገዱ ግንባታ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ውስጥ መጠናቀቅ እንዲችል ትብብር እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡