ሚኒስትሩ ስምምነቱ ሀገራቱ በጋራ ለመልማት እንደሚያስችል ገለጹ

ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን ከአጥኚ ቡድኖቹ ጋር ለመስራት መፈራረማቸው ሀገራቱ በመተማመን ላይ የተመሰረተ በጋራ ለመልማት የሚያስችል መሆኑን የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚንስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሳ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ እንደገለጹት ጥናቱ የግድቡ የውኃ አያያዝ፣ አለቃቀቅ፣ የውሃ ፍሰት መጠን ና ግድቡ በታችኛው የተፋሰሱ አገሮች ላይ ሊያመጣ የሚችለው ተጽዕኖ ዙሪያ የሚከናወን በመሆኑ በመተማመን በጋራ ለመልማትና ለበለጠ ትብብር አቅም የሚፈጥር ነው፡፡

ይህም ከግድቡ ግንባታና ጥናቱ ጎን ለጎን እንደሚጓዙና 6 ሺህ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት ሥራውም በሂደት እንደሚቀጥል ሚንስትሩ አስረድተዋል፡፡

ጥናቱን ለማድረግ የሁለት ወር ቅድመ ዝግጅት የሚያድርጉ ሲሆን፤ ዋናው ጥናት በአስራ አንድ ወራት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ነው የተገለጸው፡፡

ጥናቱ 70 በመቶውን ቢ አር ኤል ኢንጂነሮች እና 30 በመቶውን ደግሞ አርቴሊያ በተባሉት የፈረንሳይ ድርጅቶች እንደሚከናወን ጠቁመዋል ፡፡

ለጥናቱ የተመደበው 4 ነጥብ 45 ሚሊየን ዩሮ ደግሞ ሶስቱም ሀገራት እንደሚሸፍኑት ገልጸዋል ፡፡

በጥናቱ ከሶስቱም ሀገራት የሚሰበሰቡት መረጃዎች ትክክለኛነት የሶስትዮሽ ብሔራዊ ኮሚቴው  እንድሚገመገሙም አመልክተዋል ፡፡

ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ጥናቱን ከሚያከናውኑ የፈረንሳይ ኩባንያዎች ጋር በትላንትናው ዕለት በሱዳን ካርቱም ስምምነት እደተፈራረሙ ይታወሳል፡፡

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በ2008 በጀት ዓመት መጨረሻ ላይ 51 በመቶ መድረሱን ለማወቅ መቻሉን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል፡፡