ኢትዮጵያና ቻይና ትብብራቸውን ይበልጥ ለማሳደግ ተስማሙ

የቻይናው  ፕሬዚዳንት ልዩ ልዑክ  ዢ ሻዎሺ አዲስ አበባ በሚገኘው የቻይና ኢምባሲ በሠጡት መግለጫ እንዳመለከቱት  ሁለቱ አገራት  በተለይ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ፣ በአቅም ግንባታ፤ በመንገድ ግንባታናየቻይናውያን ባለሃብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ስለሚያከናውኑት ኢንቨስትመንት በጋራ  ለመሥራት ተስማምተዋል ።

ዢ ሻዎሺ እንደተናገሩት  በተለይ ሁለቱ አገራት በተለይም የሳይንስና ቴክኖሎጂን  ለመደገፍ  የተለያዩ  የማሳያ ኢንዱስትሪዎችን እንዲገነቡ፣ የቃሊቲን የቀለበት መንገድ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግና  በቻይና የግል ኢንተርፕራይዞችበኢትዮጵያ የግል ኢንዱስትሪ መንደሮች መዋለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ የሚያስችል የትብብር ስምምነት ፈጽመዋል ።

በተጨማሪም ሁለቱ አገራት በመሠረተ ልማት፣ የምርት አቅምን በማሳደግና በጤና ኮሚኒኬሽን ዘርፎች  ትብብር ለማድረግ መስማማታቸውን የጠቆሙት ዢ ሻዎሺ  ስምምነቶች  የአገራቱን  ትብብር  ይበልጥ ያሳድገዋል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል ።  

የቻይናው ፕሬዚዳንት ዢ ፒንግ በጁሃንስበርግ የአፍሪካ-ቻይና ስብሰባ ላይ በአፍሪካ  አሥር አበይት የልማት ዕቅዶችን ተግባራዊ ለማድረግ  ቃል ማግባታቸውን  ያስታወሱት ዢ ሻዋሺ በኢትዮጵያ የዕቅዱ አካላት የሆኑት የባቡር መሥመር ግንባታና ኢንዱስትሪዎችን የማስፋፋት ሥራዎችን እውን እየሆኑ ይገኛሉ ብለዋል ።

ኢትዮጵያ የቻይና ጠንካራና ስትራቴጂክ አጋር መሆኗን  ዢ ሻዎሺ ገልጸው  እስካሁን  ዘርፈ ብዙ የሆኑ የሁለቱ አገራት ግንኙነት  በኢትዮጵያ   የተለያዩ ክፍሎች የሚገኝ ህብረተሰብን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን  አስረድተዋል ።

ኢትዮጵያ በቻይና ድጋፍ 758 ኪሎሜትር የሚረዝምና በዘመናዊነቱ በአፍሪካ  መጀመሪያው የሆነውን የአዲስ አበባ -ጅቡቲ  የባቡር  መሥመር በትናንትናው ዕለት አስመርቃለች ።