የጀርመን መንግስት በመደበው 27 ሚሊየን ዩሮ በአዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት ዋና ፅህፈት ቤት ግቢ የተገነባው የጁሊየስ ኔሬሬ የሰላምና ፀጥታ ህንፃ ዛሬ ተመረቀ።
ህንፃውን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ፣ የጀርመኗ መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል እና የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ኒኮሳዛና ዲላሚኒ ዙማ በጋራ መርቀውታል።
ህንፃውን የአፍሪካ ህብረት የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት የሚጠቀመው ሲሆን፥ የአህጉሪቱ የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና የሰላም ማስጠበቅ ተልእኮዎች የሚመሩበት ዋና ፅህፈት ቤት ሆኖ ያገለግላል ተብሏል።
ህንፃው የመሰብሰቢያ አዳራሽ፣ የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት የሚወያይበት አዳራሽ፣ በአህጉሪቱ የሚያጋጥሙ አስቸኳይ የፀጥታ ሁኔታዎች የሚታዩባቸው ክፍሎች እና ቤተ መፅሃፍትን ያካተተ ሲሆን፥ 360 ሰራተኞችን ማስተናገድ የሚችሉ ቢሮዎችን ያካተተ ነው።
ህንፃው ህብረቱ በመላው አህጉሪቱ ሰላምና ፀጥታ ለማስፈን ለሚያደርገው ጥረት ስኬት ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ተብሎ ታምኗል-(ኤፍ ቢ ሲ) ።