በባቡር መሰረተ ልማት ዘርፍ የሚፈለገውን ውጤት ለማስመዝገብ ብቃት ያላቸው ወጣት መሀንዲሶችን ለማፍራት በደንብ መስራት እንደሚገባ ተመለከተ፡፡
የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽንና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዛሬ በኢሊሌ ሆቴል ባዘጋጁት የአፍሪካ የባቡር ልማት ጉባዔ እንደተመለከተው በባቡር ዘርፍ ከቴክኖሎጂ ሽግግር በተጓዳኝ ወጣት የባቡር መሀንዲሶችን በብዛት ማፍራት ይገባል፡፡
የአገሪቱን ልማት ለማፋጠን ትልቅ ሚና የሚጫወተውን የባቡር ልማት ዘርፍ በሚፈለገው ጥራትና ፍጥነት ለማስኬድ ለወጣት መሀንዲሶች ትኩረት መስጠት እንደሚገባ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ጌታቸው መንግስቴ ገልፀዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑና ዩኒቨርሲቲው በአቅም ግንባታ ዘርፍ የጀመሩትን የጋራ ጉዞ በደንብ እንዲያጠናክሩም በአፅንኦት አስገንዝበዋል፡፡
የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማፋጠን የባቡር ዘርፍ ሚና ከፍተኛ መሆኑንም ነው ያስረዱት፡፡
የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር ኢንጂነር ጌታቸው በትሩ በባቡር ቴክኖሎጂ ዘርፍ ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎች በውጭና በአገር ውስጥ በማሰልጠን ዘርፉን በሚፈለገው ጥራትና ፍጥነት ለማስኬድ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ወጣት መሀንዲሶች ለዘርፉ ዕድገትና መበልፀግ ዋናው ሞተር በመሆናቸው ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገልፀዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ ከትምህርት ሚኒስቴርና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባከናወነው የአቅም ግንባታ ሥራ በርካታ ወጣቶች ዘርፉን እንዲቀላቀሉ ማድረጉን አስረድተዋል፡፡
ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት ተመርቀው ለወጡ ወጣቶች ለሁለት ወራት የሥራ ላይ ስልጠና በመስጠት በተለያዩ የባቡር መሰረተ ልማት ቀጣናዎች ላይ 380 ወጣቶች እንዲሳተፉ ዕድል ተፈጥሯል ብለዋል-ዋና ሥራ አስፈፃሚው ፡፡
‹‹ቀደም ሲል 40 ወጣት መሃንዲሶች በሩስያና በቻይና በባቡር ምህንድስና ዘርፍ በሁለተኛ ዲግሪ ተመርቀዋል›› ነው ያሉት ኢንጂነር ጌታቸው ፡፡
በርከት ያሉ የኮርፖሬሽኑ ሠራተኞችና ወጣቶች በቻይናና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አቅማቸውን እንዲያሳድጉ ኮርፖሬሽኑ ወጭያቸውን በመሸፈን ማሰልጠኑን አንስተዋል ፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በየቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኢሳያስ ገብረ ዮሐንስ በበኩላቸው ፤በዩኒቨርሲቲው በባቡር ቴክሎጂ ዘርፍ በሲቪል፣በኤሌክትሪካል ምህንድስናና በተያያዥ ዘርፎች 300 ወጣቶችን በሁለተኛ ዲግሪ አሰልጥኖ ማውጣቱን አስታውቀዋል፡፡
በሠልጣኞችም ለዘርፉ የሚረዱ ከ300 በላይ ጥናታዊ ፅፉፎች መሰራታቸውን ጠቁመው አሁንም በትምህርት ላይ ያሉ ሰልጣኞች መኖራቸውን አመልክተዋል፡፡
‹‹ዩኒቨርሲቲው በባቡር ቴክኖሎጂ ዘርፍ የልቀት ማዕከል ሆኖ እንዲያገለግል ተመርጧልም ነው ያሉት ፡፡
በዓለም ባንክ የሚደገፍ የአፍሪካ የባቡር ልማት ዘርፍ የትምህርትና የምርምር ተቋም ተቋቁሟል›› ሲሉ አስታውቀዋል ፡፡
በአምስት ዓመት 521 መሃንዲሶችን ለማሰልጠን 40 ሚሊዮን ብር ወጭ እንደሚደረግ በመድርኩ ተመልክቷል፡፡
የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር 756 ኪሎ ሜትር ሥራ ተጠናቆ በቅርቡ መመረቁንና መንግስት እስከ 2012 ዓመተ ምህረት ድረስ 5 ሺ ኪሎ ሜትር የባቡር መስመር ለመዘርጋት አቅዶ እየሰራ እንደሚገኝ ይታወቃል ፡፡