ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ያካበተውን ሰፊ ልምድ በመጠቀም በተለያዩ ፍርማቶች መረጃዎችን በራሱ የቴሌቭዥን ጣቢያ ለህዝቡ ለማድረስ ታጥቆ መነሳቱን ገለፀ፡፡
ማዕከሉ የቴሌቭዥን ስርጭት ፍቃዱን ትናንት በሸራተን አዲስ በተካሄደ የፍቃድ አሰጣጥ ሥነ ሥርዓት ላይ ከኢትዮጵያ ብሮድ ካስት ባለሥልጣን ጋር በመፈራረም ፍቃዱን ተቀብሏል፡፡
ዋልታ ወቅታዊ፣ትክክለኛና ሚዛናዊ መረጃዎችን በማጠናቀርና በማደራጀት በማራኪ አቀራረብ ለህብረተሰቡ ለማድረስ አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቁን የማዕከሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተተካ በቀለ ተናግረዋል፡፡
በዜና፣በፕሮግራምና በዘጋቢ ፊልም ፎርማቶች ህብረተሰቡን የሚያስተምሩ፣ የሚያሳውቁና የሚያዝናኑ መረጃዎችን ለአየር በማብቃት አማራጭ የቴሌቭዥን ጣቢያ በመሆን ይሰራል ብለዋል፡፡
ማዕከሉ ለስርጭት አገልግሎት የሚውል ዘመናዊ ስቱዲዮ የመገንባትና ዘመኑ የደረሰባቸው የፕሮዳክሽን መሳሪያዎችን የመግዛት ሥራዎችን ማናወኑን አቶ ተተካ ገልፀዋል፡፡
ሥርጭቱን በብቃትና በጥራት ለማስተላለፍ በዘርፉ የሰለጠኑና በቂ ልምድ ያላቸው ከ70 በላይ ወጣት ባለሙያዎችን በመቅጠር ሙያዊ ሥልጠና እንዲወስዱም ተደርጓል፡፡
ጣቢያውን ጠንካራ ለማድረግ ለስርጭቱ የሚጠቅሙ የተለያዩ የመጠባበቂያ የፕሮዳክሽን ክምችት (ባክሎግ) የማዘጋጀት ሥራ መሰራቱን አቶ ተተካ አስገንዝበዋል፡፡ ማዕከሉ ላለፉት 15 ዓመታት የቴሌቭዥን አገልግሎቱን በብቃት ለመወጣት አቅሙን ሲገነባ መቆየቱንም ነው የተናገሩት፡፡
የተለያዩ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ባህል፣ታሪካዊና የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን በጥራትና በማራኪ አቀራረብ ዘጋቢ ፊልም በመስራት ለአድማጭ ተመልካች ሲያቀርብ መቆየቱን አቶ ተተካ ገልፀዋል፡፡ በአገሪቱ ውስጥ የሚከናወኑ የሠላም፣የልማትና የዲሞክራሲ እንቅስቃሴዎችንም ለህብረተሰቡ ሲያደርስ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡
ዋልታ ፍቃድ ማግኘቱ ጣቢያውን ሲጠብቁ አድማጭ ተመልካቾችና ለማዕከሉ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና ሠራተኞች ትልቅ ብስራ መሆኑን የማዕከሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተተካ በቀለ ተናግረዋል፡፡ በቅርብ ጊዜም ስርጭቱን ይጀምራል ብለዋል፡፡
በራሱ ጣቢያ ወደ ህዝብ መድረሱ ቀደም ሲል ሲያከናውናቸው የነበሩትን ሥራዎች በስፋት፣በተጠናከረና በተደራጀ መልኩ ለመስራት ትልቅ አቅም እንደሚሆነው ዋና ሥራ አስኪያጁ ገልፀዋል፡፡
‹‹ለጣቢያው መጠናከር የህብረተሰቡ ድርሻ የላቀ ነው›› ያሉት አቶ ተተካ ህዝቡ ጥቆማዎችን በማድረስና አስተያየቶችን በመስጠት እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ሰፊ የመረጃ ምንጭ በመሆንም የበኩሉን አስተዋፅዖ እንዲያበረክት አሳስበዋል፡፡
ከዋልታ በተጨማሪ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እና አርኪ ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ በሀገሪቱ የመጀመሪያ የሆነውን የንግድ የቴሌቪዥን ስርጭት ፈቃድ ተቀብለዋል፡፡