የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ግንባታ መጠናቀቅ የተጀመሩ ታላላቅ ፕሮጄክቶችን በማፋጠን ለበለጠ ስራ እንደሚያነሳሳ ጎብኝዎች ገለጹ፡፡
የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዛሬ ባዘጋጀው የኢትዮ -ጁቡቲ ባቡር መስመር ጉብኝት የሕዝብ ግንኑነት ኃላፊዎች፣ አርቲስቶች፣ የኃይማኖት ተቋማት፣ የዳያስፖራ ማሕበራትና ጋዜጠኞች ተሳታፊ ሆነዋል ፡፡
ተሳታፊዎቹ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደለጹት፤ የፕሮጄክቱ መጠናቀቅ በተለይም የታላቁን ሕዳሴ ግድብ ጨምሮ ሀገሪቷ እያከናወነቻቸው ያሉትን ታላላቅ ልማቶች ለማጠናቀቅና በቀጣይ ሌሎች ፕሮጄክቶችን ለመገንባት ዓቅም ይፈጥራል፡፡
ከጎብኝዎቹ ውስጥ ወይዘሪት ስንቅነሽ ሞላ ፕሮጀክቱ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ዕድገትና ህዳሴዋን ለማስቀጠል፣ መዋቅራዊ ሽግግርን ለማፋጠን እንዲሁም ድህነትን ለመቀነስ የሚኖረው ሀገራዊ ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ገልጻለች።
የባቡር ፕሮጄክቱ ከፍተኛ ወጪ ተደርጎበት የተገነባ በመሆኑ ሕብረተሰቡ አገልግሎቱን ሲያገኝ ለባቡሩ ጥንቃቄና ጥበቃ ሊያድርግለት እደሚገባም ወይዘሪት ስንቅነሽ አስረድታለች፡፡
የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማሕበር ፕሬዝዳንት አቶ ዳዊት ይፍሩ በበኩላቸው ሙዚቀኞች በሀገሪቱ ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ በማድረግ የልማት አጋር እንደነበሩ ጠቁመው ፤ አሁንም ተሳትፎው ይበልጥ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
የሀገሪቱ ፈጣን ኢኮኖሚ በማስቀጠል በ2017 መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለማሰለፍ የምታደርገውን ጥረት ለማሳካት የባቡር መስመሩ ድርሻው የጎላ እንደሆነ የገለጹት ደግሞ አቶ ስለሺ ዘገዬ ናቸው ፡፡
አቶ ስለሺ አክለውም በሀገሪቱ እየተከናወኑ ያሉትን ሌሎች ግንባታዎች ላይ ሕብረተሰቡ እያደረገው ያለውን ተሳትፎ እንዲያጠናክር የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ፕሮጄክት ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር አስረድተዋል ፡፡
የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደረጄ ተፈራ ለጎብኝዎቹ ባደረጉት ገለጻ፤ ከአዲስ አበባ ወደ ጅቡቲ በተሽከርካሪ ለመሄድ ከ 4ቀናት በላይ ይወስድ የነበረው የአገሪቱ የወጭና የገቢ ምርቶች በ10 ሰዓታት ውስጥ እና በዝቅተኛ ወጭ ለማጓጓዝ የሚያስችል መሆኑን አንስተዋል፡፡
በ3 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር ወጪ የተገነባው ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ በዓለም ገበያ ላይ የሚኖራትን ተወዳዳሪነት የሚያሳድግ መሆኑን አስረድተዋል ።
ኢትዮጵያን ከጅቡቲ የሚያገናኘው የ758 ኪሎ ሜትር የባቡር መስመሩ በቅርቡ ተመርቆ በሙኮራ ሂደት ላይ መሆኑ ይታወቃል ።