በበጀት ዓመቱ ለህዳሴ ግድብ 2 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዷል

በተያዘው በጀት ዓመት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሁለት ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱ ተገለፀ፡፡

የግድቡን ግንባታ በተያዘለት ዕቅድ ለማስኬድ ገንዝብ የማሰባሰብ ሥራውን ማጠናከር እንደሚገባ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪና የመገናኛ እና ኢንፎርሜሽን ሚኒስትር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ለዋልታ ተናግረዋል፡፡

‹‹ባለፉት አምስት ዓመታት ከ28 ቢሊየን ብር በላይ ገንዘብ ማሰባሰብ ተችሏል›› ያሉት ሚኒስትሩ በተያዘው በጀት ዓመትም ከሁለት ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ ግንባታውን በተያዘው ፍጥነት የማስኬድ ዕቅድ ተይዟል ብለዋል፡፡

ገንዘቡን ለማሰባሰብ የተነደፉ ስልቶች አሉ ወይ) በሚል ዋልታ ላቀረበላቸው ጥያቄ ‹‹ 8100 ኤ፣ የቦንድ ሽያጭ፣ የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ጨዋታዎችና ፕሮግራሞች ተግባራዊ ይደረጋሉ›› ብለዋል፡፡

ከገንዘብ ማሰባሰቡ በተጓዳኝ ሠፊና ጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራ እንደሚከናወን ዶክተር ደብረፅዮን ተናግረዋል፡፡ የዳያስፖራውን ተሳትፎ ለማሳደግና ለማጠናከርም ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል፡፡

ዶክተር ደብረፅዮን እንዳሉት ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ህዝብ የዲፕሎማሲ ልዑካን በሱዳንና በግብፅ ያካሄዱት ጉብኝት ጥሩ ውጤት አስመዝግቧል፡፡ ባለፈው ዓመት የሱዳን ህዝብ የዲፕሎማሲ ልዑካን በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት የዲፕሎማሲ ሥራ ጥረት ነው፡፡ በቀጣይም የዲፕሎማሲ ጥረቱ ይበልጥ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

‹‹አጠቃላይ የግድቡ ሥራ 54 በመቶ ደርሷል፡፡ 750 ሜጋ ዋት ኃይል የሚያመነጩ ተርባይኖቹን የመግጠም ሥራ በቅርቡ ይከናወናል›› ያሉት  ሚኒስትሩ ተረባይኖቹም የግድቡ ሥፍራ መድረሳቸውን ነው የጠቆሙት፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ሰሞኑን ባካሄደው 8ኛ መደበኛ ጉባኤ ባለፉት አምስት አመታት ከ28 ቢሊየን ብር በላይ መሰብሰቡን አስታውሶ ይህም ይህም ቃል ከተገባው 49 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ከግማሽ በላይ መሆኑን ነው ያመለከተው።

በ2008 በጀት አመት 12 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ቃል ተገብቶ 8 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን ጠቁሞ ይህም ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ የተሰበሰበበት ዓመት መሆኑን በሪፖርቱ አስረድቷል፡፡ ከዲያስፖራው ማህበረሰብም እስካሁን 2 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር መሰብሰቡ ተመልከቷል፡፡