የመስኖና የኃይል ማመንጫ ግድቦች ባሉባቸው ተፋሰሶች 30 ነጥብ 6 ሚሊየን ችግኞች መተከላቸውን የውሃ ፣መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ገለጸ ፡፡
የሚኒስቴር መስሪያቤቱ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ብዙነህ ቶልቻ እንዳመለከቱት ፤ ባሳለፍነው ክረምት በተከዜ፣ በግልገል ጊቤ፣ በስምጥ ሸለቆና በጣና በለስ ተፋሰሶች በ5 ሺ 547 ሄክታር ላይ 30 ነጥብ 6 ሚሊየን ችግኞች ተከላ ተከናውነዋል፡፡
ይህም በስነ-ሕይወታዊ መስክ ተራቁተው የነበሩ አከባቢዎች ወደ ነበሩበት እንደሚለሱ ከማድረጉም በላይ የሃይል ማመንጫ ግድቦቹ በደለል እንዳይሞሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው አስረድተዋል ፡፡
ባሳለፍነው ዓመት የመስኖና የሃይል ማመንጫ ግድቦች ባሉባቸው ተፋሰሶች በ134 ሺ 759 ሄክታር መሬት ላይ የተለያዩ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ለመስራት ታቅዶ 130 ሺ 446 ሄክታር መሬት ማልማት መቻሉን አስታውቀዋል ፡፡
በተያዘው አዲስ በጀት ዓመትም ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል ፡፡